ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 4:17-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ሰብል እንደሚጠብቁ ሰዎች ይከቧታል፤በእኔ ላይ ዐምፃለችና፤’ ”ይላል እግዚአብሔር።

18. “የገዛ መንገድሽና ተግባርሽ፣ይህን አምጥቶብሻል፤ይህም ቅጣትሽ ነው፤ምንኛ ይመራል!እንዴትስ ልብ ይሰብራል!”

19. ወይ አበሳዬ! ወይ አበሳዬ!ሥቃይ በሥቃይ ላይ ሆነብኝ፤አወይ፣ የልቤ ጭንቀት!ልቤ ክፉኛ ይመታል፤ዝም ማለት አልችልም፤የመለከትን ድምፅ፣የጦርነትንም ውካታ ሰምቻለሁና።

20. ጥፋት በጥፋት ላይ ይመጣል፤ምድሪቱም በሞላ ባድማ ትሆናለች፤ድንኳኔ በድንገት፣መጠለያዬም በቅጽበት ጠፋ።

21. እስከ መቼ የጦርነት ዐርማ እመለከታለሁ?እስከ መቼስ የመለከት ድምፅ እሰማለሁ?

22. “ሕዝቤ ተላሎች ናቸው፤እኔን አያውቁኝም።ማስተዋል የጐደላቸው፣መረዳትም የማይችሉ ልጆች ናቸው።ክፋትን ለማድረግ ጥበበኞች፤መልካም መሥራት ግን የማያውቁ።”

23. ምድርን ተመለከትሁ፤እነሆ ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች፤ሰማያትንም አየሁ፣ብርሃናቸው ጠፍቶአል።

24. ተራሮችን ተመለከትሁ፣እነሆ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ኰረብቶችም ሁሉ ተናጡ።

25. አየሁ፤ ሰው አልነበረም፤የሰማይ ወፎች ሁሉ በረው ጠፍተዋል።

26. ተመለከትሁ፤ እነሆም፣ ፍሬያማው ምድር በረሓ ሆነ፤ከተሞቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት፣ከብርቱ ቍጣው የተነሣ ፈራረሱ።

27. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፤ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም።

28. ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፤ሰማያትም በላይ ይጨልማሉ፤ተናግሬአለሁ፤ ሐሳቤን አልለውጥም፤ወስኛለሁ፤ ወደ ኋላም አልልም።

29. ከፈረሰኞችና ከቀስተኞች ጩኸት የተነሣ፣ከተማ ሁሉ ይሸሻል፤አንዳንዶች ደን ውስጥ ይገባሉ፤ሌሎችም ቋጥኝ ላይ ይወጣሉ፤ከተሞች ሁሉ ባዶ ቀርተዋል፤የሚኖርባቸውም የለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 4