ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 39:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢየሩሳሌም የተያዘችው እንዲህ ነበር፤ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አሰልፎ በመምጣት ኢየሩሳሌምን ከበባት።

2. በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ አንደኛው ዓመት በአራተኛው ወር፣ በወሩም በዘጠነኛው ቀን የከተማዪቱ ቅጥር ተሰበረ።

3. የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ፦ የሳምጋሩ ኤርጌል ሳራስር፣ ዋና አዛዡ ናቦሠርሰኪም፣ ከፍተኛው ሹም ኤርጌል ሳራሳር እንዲሁም ሌሎቹ የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ ገብተው በመካከለኛው በር ተቀመጡ።

4. የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና ወታደሮቹ ሁሉ እነርሱን ባዩ ጊዜ ሸሹ፤ በሌሊት በንጉሡ አትክልት ስፍራ በኩል አድርገው በሁለቱ ቅጥር መካከል ከከተማዪቱ ወጡ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።

5. የባቢሎን ሰራዊት ግን ተከትሎ አሳደዳቸው፣ በኢያሪኮም ሜዳ ደርሶባቸው ሴዴቅያስን ያዘ፤ ማርከውም በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፤ በዚያም ፍርድ ወሰነበት።

6. የባቢሎንም ንጉሥ በሪብላ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች፣ አባታቸው እያየ ዐረዳቸው፤ የይሁዳን መሳፍንት ሁሉ ገደላቸው፤

7. የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ ወደ ባቢሎን ሊወስደውም በናስ ሰንሰለት አሰረው።

8. ባቢሎናውያን ቤተ መንግሥቱንና የሕዝቡን ቤት በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 39