ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 37:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የኢዮስያስን ልጅ ሴዴቅያስን በይሁዳ ላይ አነገሠው፤ እርሱም በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፈንታ ነገሠ።

2. ነገር ግን እርሱም ሆነ መኳንንቱ የምድሪቱም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ አማካይነት የተነገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።

3. ንጉሡ ሴዴቅያስም፣ “ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ” በማለት የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ።

4. ኤርምያስ ገና እስር ቤት ስላልገባ፣ በሕዝቡ መካከል እንደ ልቡ ይወጣና ይገባ ነበር።

5. የፈርዖንም ሰራዊት ከግብፅ ወጥቶ ነበርና ኢየሩሳሌምን ከበው የነበሩት ባቢሎናውያን ይህን ሲሰሙ ኢየሩሳሌምን ለቀው ሄዱ።

6. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

7. “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትጠይቁኝ ዘንድ ወደ እኔ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሰራዊት ወደ ገዛ አገሩ ወደ ግብፅ ይመለሳል፤

8. ባቢሎናውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይወጓታል፤ ይዘውም ያቃጥሏታል።’

9. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ባቢሎናውያን በእርግጥ ትተውን ይሄዳሉ’ ብላችሁ አታስቡ፤ አይሄዱምና ራሳችሁን አታታሉ።

10. የሚዋጋችሁን የባቢሎናውያንን ሰራዊት ሁሉ አሸንፋችሁ፣ ቍስለኞች ብቻ በድንኳኖቻቸው ውስጥ ቢቀሩ እንኳ፤ እነዚህ ሰዎች መጥተው ይህችን ከተማ ያቃጥሏታል።”

11. የባቢሎን ሰራዊት ከፈርዖን ጭፍራ የተነሣ ከኢየሩሳሌም ከወጣ በኋላ፣

12. ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን ድርሻ ለመካፈል፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ተነሣ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 37