ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 33:17-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ከዳዊት ዘር በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይታጣም፤

18. ሌዋውያን ከሆኑት ካህናትም የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእህል ቍርባን ለማቃጠልና ሌላውንም መሥዋዕት ለመሠዋት ሁል ጊዜ በፊቴ የሚቆም ሰው አይታጣም።’ ”

19. የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

20. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለቀንና ለሌሊት የወሰንሁትን ሥርዐት በማፋለስ ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዳይፈራረቁ ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፣

21. በዚያ ጊዜ ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋር የገባሁትን ኪዳን፣ እንዲሁም በፊቴ በክህነት ከሚያገለግሉት ሌዋውያን ጋር የገባሁትን ኪዳን ማፍረስ ይቻላል፤ ዳዊትም ከእንግዲህ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ዘር አይኖረውም።

22. የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እንዲሁም በፊቴ የሚቆሙትን ሌዋውያን እንደማይቈጠሩ እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደማይሰፈር የባሕር አሸዋ አበዛቸዋለሁ።’ ”

23. የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

24. “ይህ ሕዝብ፣ ‘እግዚአብሔር፣ የመረጣቸውን ሁለቱን መንግሥታት ጥሎአል’ እንደሚሉ አላስተዋልህምን? ሕዝቤን ንቀዋል፤ እንደ ሕዝብም አልቈጠሯቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 33