ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 33:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኤርምያስ በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ በግዞት ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እርሱ መጣ፦

2. “ምድርን የፈጠራት፣ ያበጃትና የመሠረታት እግዚአብሔር፣ ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፣ እርሱ እንዲህ ይላል፤

3. ‘ወደ እኔ ጩኽ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና የማይመረመር ነገር እገልጥልሃለሁ፤’

4. የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከባቢሎናውያን ጋር ባለው ውጊያ፣ ዐፈር በመደልደልና በሰይፍ የሚደረገውን ጥቃት ለመከላከል ስለ ፈረሱት ስለዚህች ከተማ ቤቶችና ስለ ይሁዳ ነገሥታት ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤

5. ‘እነዚህ በቍጣዬና በመዓቴ በምገድላቸው ሰዎች ሬሳ ይሞላሉ፤ ስለ ክፋቷ ሁሉ ከዚህች ከተማ ፊቴን እሰውራለሁ።

6. “ ‘ይሁን እንጂ፣ ፈውስንና ጤንነትን እንደ ገና እሰጣታለሁ፤ ሕዝቤንም እፈውሳለሁ፤ በብዙ ሰላምና በርጋታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ።

7. የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ቀድሞ እንደ ነበሩት ሁኔታ አድርጌ አበጃቸዋለሁ፤

8. እኔን ከበደሉበት ኀጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ፤ በእኔ ላይ ያመፁበትንም ኀጢአታቸውን ሁሉ ይቅር እላለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 33