ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 32:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ፣ የአጎቴ ልጅ አናምኤል ወደ ዘብ ጠባቂዎቹ አደባባይ መጥቶ፣ “የመቤዠቱን ርስት የማድረጉ መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን መሬቴን ለራስህ እንዲሆን ግዛው” አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ዐወቅሁ፤

9. ስለዚህ በዓናቶት ያለውን መሬት ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብር መዝኜ ሰጠሁት።

10. በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት።

11. የስምምነቱ ዝርዝር ያለበትን፣ የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤

12. በአጎቴም ልጅ በአናምኤልና በውሉ ላይ በፈረሙት ምስክሮች ፊት እንዲሁም በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተቀምጠው በነበሩ አይሁድ ሁሉ ፊት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።

13. በእነርሱ ፊት ለባሮክ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠሁት፤

14. “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የታሸገውንና ያልታሸገውን፣ ሁለቱን የግዢ ውል ሰነዶች ለብዙ ጊዜ ሳይበላሹ እንዲቈዩ ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው።

15. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ሰዎች በዚህ ምድር ቤት፣ የዕርሻ ቦታና የወይን አትክልት ስፍራ እንደ ገና ይገዛሉ።’ ”

16. “ለኔርያ ልጅ ለባሮክ የግዢ ውሉን ከሰጠሁ በኋላ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤

17. “አቤት፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም።

18. ፍቅርና ቸርነትን ለእልፍ አእላፍ ታሳያለህ፤ ይሁን እንጂ የአባቶችን በደል ከእነርሱ በኋላ በሚነሡ ልጆቻቸው ጒያ ትመልሳለህ፤ ስምህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነ፣ ታላቅና ኀያል አምላክ ሆይ፤

19. ዕቅድህ ታላቅ፣ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ዐይኖችህ የሰው ልጆችን መንገዶች ሁሉ ያያሉ፤ ለእያንዳንዱም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።

20. በግብፅ ታምራትንና ድንቆችን አደረግህ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሰው ልጆች ሁሉ መካከል እንደዚያው እያደረግህ ዛሬም ስምህ ገናና ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 32