ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 32:22-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ለአባቶቻችን ልትሰጣቸው የማልህላቸውን፣ ማርና ወተት የምታፈሰውን ይህችን ምድር ሰጠሃቸው፤

23. ወደዚያም ገብተው ወረሷት፤ ነገር ግን አልታዘዙህም፤ ሕግህንም አልጠበቁም፤ እንዲያደርጉት ያዘዝሃቸውን ከቶ አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ሁሉ ጥፋት በላያቸው አመጣህ።

24. “እነሆ፤ ከተማዪቱን ለመያዝ የዐፈር ድልድል በዙሪያዋ ተሠርቶአል፤ ከሰይፍ፣ ከራብና ከቸነፈር የተነሣ ከተማዪቱን ለሚወጓት ለባቢሎናውያን ዐልፋ ልትሰጥ ነው፤ እንደምታየውም የተናገርኸው እየተፈጸመ ነው።

25. አንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተማዪቱ ለባቢሎናውያን አልፋ እየተሰጠች፣ ‘መሬቱን በብር ግዛ፤ ግዢውንም በምስክሮች ፊት ፈጽም’ ትለኛለህ።”

26. ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

27. “እነሆ፤ እኔ የሰው ልጆች ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ የሚያቅተኝ ነገር አለን?

28. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እነሆ፤ ይህቺን ከተማ ለባቢሎናውያንና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።

29. ከተማዪቱን የሚወጓት ባቢሎናውያን ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤ ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቡ በየሰገነቱ ላይ ለበኣል ያጠኑባቸውንና ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀረቡባቸውን ቤቶች ጭምር ያነዳሉ።

30. “የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ከክፉ ነገር በቀር በፊቴ አንዳች በጎ ነገር አልሠሩም፤ በእርግጥም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው ሥራ አስቈጡኝ፤ ይላል እግዚአብሔር።

31. ይህች ከተማ፣ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከፊቴ እንዳስወግዳት ቍጣ ዬንና መዓቴን አነሣሥታለች፤

32. የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብዕጠ እነርሱ፣ ነገሥታታቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸው፣ ካህናታቸው፣ ነቢያታቸው፣ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ባደረጉት ክፋት ሁሉ አስቈጡኝ።

33. ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፤ ደጋግሜ ባስተምራቸውም አይሰሙም፤ ተግሣጽም አይቀበሉም።

34. ስሜ በተጠራበት ቤት አስጸያፊ ጣዖታቸውን አቆሙ፤ አረከሱትም።

35. ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ ይሠው ዘንድ በሄኖም ሸለቆ ለበኣል መስገጃ ኰረብቶችን ሠሩ፤ ነገር ግን ይሁዳን ኀጢአት ለማሠራት እንደዚህ ያለውን አስጸያፊ ተግባር እንዲፈጽሙ እኔ አላዘዝሁም፤ ከቶም አላሰብሁም።

36. “ ‘በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፋ ትሰጣለች’ ስላልሃት ስለዚህች ከተማ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

37. “በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ በሰላምም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ።

38. እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።

39. ለእነርሱና ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው ዘወትር ይፈሩኝ ዘንድ፣ አንድ ልብ አንድም ሐሳብ እሰጣቸዋለሁ።

40. መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈ ጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 32