ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 32:10-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት።

11. የስምምነቱ ዝርዝር ያለበትን፣ የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤

12. በአጎቴም ልጅ በአናምኤልና በውሉ ላይ በፈረሙት ምስክሮች ፊት እንዲሁም በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተቀምጠው በነበሩ አይሁድ ሁሉ ፊት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።

13. በእነርሱ ፊት ለባሮክ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠሁት፤

14. “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የታሸገውንና ያልታሸገውን፣ ሁለቱን የግዢ ውል ሰነዶች ለብዙ ጊዜ ሳይበላሹ እንዲቈዩ ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው።

15. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ሰዎች በዚህ ምድር ቤት፣ የዕርሻ ቦታና የወይን አትክልት ስፍራ እንደ ገና ይገዛሉ።’ ”

16. “ለኔርያ ልጅ ለባሮክ የግዢ ውሉን ከሰጠሁ በኋላ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤

17. “አቤት፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም።

18. ፍቅርና ቸርነትን ለእልፍ አእላፍ ታሳያለህ፤ ይሁን እንጂ የአባቶችን በደል ከእነርሱ በኋላ በሚነሡ ልጆቻቸው ጒያ ትመልሳለህ፤ ስምህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነ፣ ታላቅና ኀያል አምላክ ሆይ፤

19. ዕቅድህ ታላቅ፣ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ዐይኖችህ የሰው ልጆችን መንገዶች ሁሉ ያያሉ፤ ለእያንዳንዱም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።

20. በግብፅ ታምራትንና ድንቆችን አደረግህ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሰው ልጆች ሁሉ መካከል እንደዚያው እያደረግህ ዛሬም ስምህ ገናና ነው።

21. በታምራትና በድንቅ፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ እጅግ በሚያስፈራም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብፅ አወጣህ።

22. ለአባቶቻችን ልትሰጣቸው የማልህላቸውን፣ ማርና ወተት የምታፈሰውን ይህችን ምድር ሰጠሃቸው፤

23. ወደዚያም ገብተው ወረሷት፤ ነገር ግን አልታዘዙህም፤ ሕግህንም አልጠበቁም፤ እንዲያደርጉት ያዘዝሃቸውን ከቶ አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ሁሉ ጥፋት በላያቸው አመጣህ።

24. “እነሆ፤ ከተማዪቱን ለመያዝ የዐፈር ድልድል በዙሪያዋ ተሠርቶአል፤ ከሰይፍ፣ ከራብና ከቸነፈር የተነሣ ከተማዪቱን ለሚወጓት ለባቢሎናውያን ዐልፋ ልትሰጥ ነው፤ እንደምታየውም የተናገርኸው እየተፈጸመ ነው።

25. አንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተማዪቱ ለባቢሎናውያን አልፋ እየተሰጠች፣ ‘መሬቱን በብር ግዛ፤ ግዢውንም በምስክሮች ፊት ፈጽም’ ትለኛለህ።”

26. ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

27. “እነሆ፤ እኔ የሰው ልጆች ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ የሚያቅተኝ ነገር አለን?

28. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እነሆ፤ ይህቺን ከተማ ለባቢሎናውያንና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 32