ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 32:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥረኛው ዓመት፣ ይኸውም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዐሥራ ስምንተኛ ዘመነ መንግሥት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤

2. በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ከቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተዘግቶበት ነበር።

3. የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም እንዲህ በማለት አሳስሮት ነበር፤ “እንዴት እንደዚህ ያለ ትንቢት ትናገራለህ? ‘እግዚአብሔር፤ “ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።

4. የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፎ ይሰጣል፤ ፊት ለፊትም ያነጋግረዋል፤ በዐይኖቹም ያየዋል እንጂ ከባቢሎናውያን እጅ አያመልጥም።

5. ሴዴቅያስንም ወደ ባቢሎን ይወስደዋል፤ በፍርዴ እስከምጐበኘውም ድረስ በዚያ ይቈያል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ከባቢሎናውያን ጋር ብትዋጉ አይሳካላችሁም” ይላል’ ትላለህ።”

6. ኤርምያስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ አለ፦

7. “የአጎትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፣ ‘የመቤዠት መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በዓናቶት ያለውን መሬቴን ግዛኝ’ ይልሃል።”

8. እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ፣ የአጎቴ ልጅ አናምኤል ወደ ዘብ ጠባቂዎቹ አደባባይ መጥቶ፣ “የመቤዠቱን ርስት የማድረጉ መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን መሬቴን ለራስህ እንዲሆን ግዛው” አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ዐወቅሁ፤

9. ስለዚህ በዓናቶት ያለውን መሬት ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብር መዝኜ ሰጠሁት።

10. በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት።

11. የስምምነቱ ዝርዝር ያለበትን፣ የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤

12. በአጎቴም ልጅ በአናምኤልና በውሉ ላይ በፈረሙት ምስክሮች ፊት እንዲሁም በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተቀምጠው በነበሩ አይሁድ ሁሉ ፊት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።

13. በእነርሱ ፊት ለባሮክ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠሁት፤

14. “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የታሸገውንና ያልታሸገውን፣ ሁለቱን የግዢ ውል ሰነዶች ለብዙ ጊዜ ሳይበላሹ እንዲቈዩ ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው።

15. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ሰዎች በዚህ ምድር ቤት፣ የዕርሻ ቦታና የወይን አትክልት ስፍራ እንደ ገና ይገዛሉ።’ ”

16. “ለኔርያ ልጅ ለባሮክ የግዢ ውሉን ከሰጠሁ በኋላ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤

17. “አቤት፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 32