ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 3:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፣እርሷም ሄዳ ሌላ ሰው ብታገባ፣ወደ እርሷ ይመለሳልን?ምድሪቱስ ፈጽማ አትረክስምን?አንቺ ግን ከብዙ ወዳጆችሽ ጋር አመንዝረሻል፤ታዲያ አሁን ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽን?”ይላል እግዚአብሔር።

2. “እስቲ ቀና ብለሽ ጭር ያሉትን ኰረብቶች ተመልከቺ፣በርኵሰት ያልተጋደምሽበት ቦታ ይገኛልን?በበረሓ፣ እንደ ተቀመጠ ዘላን ዐረብ፣በየመንገዱ ዳር ተቀምጠሽ ወዳጆችሽን ጠበቅሽ።በዝሙትሽና በክፋትሽ፣ምድሪቱን አረከስሽ።

3. ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፤ኋለኛው ዝናብም ጠፋ።አንቺ ግን አሁንም የጋለሞታ ገጽታ አለብሽ፤ዐይንሽን በዕፍረት አልሰብር ብለሻል።

4. አሁንም ወደ እኔ ተጣርተሽ፣‘አባቴ፣ የልጅነት ወዳጄ፣

5. ሁል ጊዜ ትቈጣለህን?ቍጣህስ ለዘላለም ነውን?’ አላልሽኝም?የምትናገሪው እንዲህ ነው፤ይሁን እንጂ የቻልሽውን ክፋት ሁሉ ታደርጊያለሽ።”

6. እግዚአብሔር በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፤ “ከዳተኛዪቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ከፍ ወዳለው ኰረብታ ሁሉ ወጥታ፣ ወደ ለመለመው ዛፍ ሥር ሁሉ ሄዳ በዚያ አመነዘረች።

7. ይህን ሁሉ ካደረገች በኋላ፣ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፤ ሆኖም አልተመለሰችም፤ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አየች።

8. ለከዳተኛ ዪቱ እስራኤል ስለ ምንዝርናዋ ሁሉ የፍች ወረቀቷን ሰጥቼ አባረርኋት። ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አይታ እንዳልፈራች አየሁ፤ ወጥታም አመነዘረች።

9. በቅሌቷም ምድሪቱን አረከሰች፤ ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 3