ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 29:8-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤

9. በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር።

10. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።

11. ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ፣ እናንተንም የሚጠቅም እንጂ የሚጐዳ አይደለም።

12. እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።

13. እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤

14. እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከምርኮም እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”

15. እናንተም፣ “እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያት አስነሥቶልናል” ትላላችሁ፤

16. እግዚአብሔር ግን በዳዊት ዙፋን ላይ ስለሚቀ መጠው ንጉሥና ከእናንተ ጋር ተማርኮ ስላልሄደው ወገንህ በዚህ ከተማ ስለ ቀረው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ይላል፤

17. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን፣ ራብንና መቅሠፍትን እሰድባቸዋለሁ፤ ከመበላሸቱ የተነሣም ሊበላ እንደማይቻል እንደ መጥፎ የበለስ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ።

18. በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት አሳድዳቸዋለሁ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉ አደርጋቸዋለሁ፤ በማሳድድባቸውም ሕዝቦች ዘንድ የርግማንና የድንጋጤ፣ የመሣቂያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ፤

19. በአገልጋዮቼ በነቢያት በኩል ደጋግሜ የላክሁላቸውን ቃሌን አልሰሙምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “እናንተ ምርኮኞችም አልሰማችሁም” ይላል እግዚአብሔር።

20. “ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

21. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚነግሯችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘እነዚህን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም ዐይናችሁ እያየ ይገድላቸዋል።

22. በእነርሱ ላይ ከደረሰው የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፣ “እግዚአብሔር፣ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግብህ” ብለው ይራገማሉ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 29