ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50
  51. 51
  52. 52

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያ

1. በዚያው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንደ ነገሠ በዐራተኛው ዓመት፣ አምስተኛ ወር፣ የገባዖኑ ሰው የዓ ዙር ልጅ ነቢዩ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ አለኝ፤

2. “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ የጫነባችሁን ቀንበር እሰብራለሁ፤

3. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መልሼ አመጣለሁ።

4. የይሁዳንም ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፣ ሌሎች ከይሁዳ ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱትንም ሁሉ ወደዚህ ስፍራ እመልሳለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ የባቢሎን ንጉሥ የጫነባቸውን ቀንበር እሰብራለሁና።’ ”

5. ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት ቆመው በነበሩት ሕዝብ ሁሉ ፊት፣ ለነቢዩ ለሐናንያ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦

6. “አሜን፤ እግዚአብሔር ያድርገው፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ፣ ተማርከው የተወሰዱትንም ምርኮኞች ሁሉ ከባቢሎን በመመለስ፣ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ቃል ይፈጽም።

7. ነገር ግን ለአንተም ለዚህም ሕዝብ የምናገረውን ቃል ስማ፤

8. ከአንተና ከእኔ በፊት ጥንት የተነሡ ነቢያት፣ በብዙ አገሮችና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ጦርነት፣ ስለ ጥፋትና ስለ መቅሠፍት ትንቢት ተናግረዋል።

9. ነገር ግን ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ እግዚአብሔር በእውነት እንደላከው የሚታወቀው የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም ነው።

10. ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ ዐንገት ወስዶ ሰበረው፤

11. በሕዝቡም ፊት፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የና ቡከደናፆርን ቀንበር ከሕዝቡ ሁሉ ጫንቃ ላይ ልክ እንደዚህ እሰብራለሁ’ አለ። በዚህ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ ትቶት መንገዱን ቀጠለ።

12. ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ከሰበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

13. “ሄደህ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አንተ የዕንጨት ቀንበር ሰብረሃል፤ እኔ ግን በምትኩ የብረት ቀንበር እሠራለሁ።

14. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እንዲያገለግሉ፣ በእነዚህ ሕዝቦች ላይ የብረት ቀንበር አደርጋለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፤ በዱር አራዊት ላይ እንኳ ሥልጣን እሰጠዋለሁ።’ ”

15. ነቢዩ ኤርምያስም ለነቢዩ ሐናንያ እንዲህ አለው፤ “ሐናንያ ሆይ፤ ስማ! እግዚአብሔር ሳይልክህ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል፤

16. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ከምድር ገጽ አስወግድሃለሁ፤ በእግዚአብሔርም ላይ ዐመፅ ተናግረሃልና፣ በዚህ ዓመት ትሞታለህ።”

17. ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።