ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 22:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. በአባቱ ምትክ በይሁዳ ላይ ስለ ነገሠው፣ ከዚህ ስፍራ በምርኮ ስለ ተወሰደው፣ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ከእንግዲህ አይመለስም፤

12. ተማርኮ በሄደበት አገር ይሞታል እንጂ ይህቺን ምድር ዳግመኛ አያይም።”

13. “ቤተ መንግሥቱን በግፍ ለሚሠራ፣ሰገነቱንም ፍትሕ በማዛባት ለሚገነባ፣ወገኑን በነጻ ለሚያሠራ፣የድካሙንም ዋጋ ለማይከፍለው፣

14. ‘ባለ ትልልቅ ሰገነት፣ሰፊ ቤተ መንግሥት ለራሴ እሠራለሁ’ ለሚል ወዮለት!ሰፋፊ መስኮቶችን ያበጅለታል፤በዝግባ እንጨት ያስጌጠዋል፤ቀይ ቀለምም ይቀባዋል።

15. “በዝግባ ዕንጨት ብዛት፣የነገሥህ ይመስልሃልን?አባትህስ ፍትሕንና ጽድቅን በማድረጉ፣የሚበላውና የሚጠጣው ጐድሎት ነበርን?እነሆ፣ ሁሉም መልካም ሆነለት።

16. የድኾችንና የችግረኞችን ፍትሕ አላጓደለም፤ስለዚህም ሁሉ መልካም ሆነለት።እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለምን?”ይላል እግዚአብሔር።

17. “የአንተ ዐይንና ልብ ያረፉት ግን፣አጭበርብሮ ጥቅምን በማግኘት፣የንጹሑን ደም በማፍሰስ፣ጭቈናንና ግፍን በመሥራት ላይ ብቻ ነው።

18. ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፤“ ‘ዋይ ወንድሜ! ዋይ፣ እኅቴን!’ብለው አያለቅሱለትም።‘ዋይ፣ ጌታዬን! ዋይ፣ ለግርማዊነቱ!’ብለውም አያለቅሱለትም።

19. አህያ እንደሚቀበር ይቀበራል፤ከኢየሩሳሌም በሮች ውጪ፤ተጐትቶ ይጣላል።

20. “ሊባኖስ ላይ ወጥተሽ ጩኺ፤ድምፅሽን በባሳን አሰሚ፤በዓባሪም ሆነሽ ጩኺ፤ወዳጆችሽ ሁሉ ወድመዋልና።

21. ተመችቶሽ በነበረ ጊዜ አስጠነቀቅሁሽ፤አንቺ ግን፣ ‘አልሰማም’ አልሽ፤ከትንሽነትሽ ጀምሮ መንገድሽ ይኸው ነበር፤ቃሌንም አልሰማሽም።

22. እረኞችሽ ሁሉ በነፋስ ይወሰዳሉ፤ወዳጆችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ከክፋትሽም ሁሉ የተነሣ፣ታፍሪያለሽ፤ ትዋረጂያለሽም።

23. አንቺ፣ ‘በሊባኖስ’ ውስጥ የምትኖሪ፣መኖሪያሽን በዝግባ ዛፍ የሠራሽ ሆይ፤ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣መከራ በላይሽ ሲመጣ ጩኸትሽ እንዴት ይሆን!

24. “በሕያውነቴ እምላለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር “የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ የቀለበት ማኅተም ብትሆን እንኳ ኖሮ፣ አውልቄ እጥልሃለሁ፤

25. ሕይወትህን ለሚሿት፣ ለምትፈራቸው ለባቢሎናውያንና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

26. አንተንና የወለደችህን እናትህን ወዳልተወለዳችሁበት ወደ ሌላ አገር ወርውሬ እጥላችኋለሁ፤ በዚያም ትሞታላችሁ።

27. ልትመለሱባት ወደ ምትናፍቋት ምድር ከቶ አትመለሱም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 22