ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 22:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት ውረድ፤ ይህንም መልእክት በዚያ እንዲህ ብለህ ተናገር፤

2. ‘በዳዊት ዙፋን የተቀመጥህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተና መኳንንትህ፣ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

3. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።

4. እነዚህን ትእዛዛት በሚገባ ብትጠብቁ፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት፣ ከመኳንንታቸውና ከሕዝባቸው ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ተቀምጠው በዚህ ቤተ መንግሥት በሮች ይገባሉ፤ ይወጣሉም።

5. ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት ባትጠብቁ፣ ይህ ቤተ መንግሥት እንዲወድም በራሴ ምያለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”

6. ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤“አንተ ለእኔ እንደ ገለዓድ፣እንደ ሊባኖስ ተራራ ጫፍ ውብ ብትሆንም፣በርግጥ እንደ ምድረ በዳ፣ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች አደርግሃለሁ።

7. በነፍስ ወከፍ መሣሪያ የሚይዙትን፣አጥፊዎችን በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ።ምርጥ የዝግባ ዛፎችን ይቈርጣሉ፤ወደ እሳትም ይጥሏቸዋል።

8. “ከተለያየ አገር የመጡ ሕዝቦች በዚህች ከተማ በኩል ሲያልፉ፣ ‘እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ላይ ለምን እንዲህ አደረገ?’ እያሉ እርስ በርስ ይነጋገራሉ፤

9. ከዚያም፣ ‘የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ኪዳን ትተው ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው’ ይላሉ።”

10. ከእንግዲህ ስለማይመለስ፣የተወለደባትንም ምድር ዳግመኛ ስለማያይ፣ለተማረከው ንጉሥ አምርራችሁ አልቅሱ እንጂ፣ቀድሞ ለሞተው አታልቅሱ፤ አትዘኑም።

11. በአባቱ ምትክ በይሁዳ ላይ ስለ ነገሠው፣ ከዚህ ስፍራ በምርኮ ስለ ተወሰደው፣ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ከእንግዲህ አይመለስም፤

12. ተማርኮ በሄደበት አገር ይሞታል እንጂ ይህቺን ምድር ዳግመኛ አያይም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 22