ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 11:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. “የዚህን ኪዳን ቃል ስማ፤ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሰዎች ንገራቸው፤

3. የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው፤ ‘ለዚህ ኪዳን ቃል የማይታዘዝ ሰው የተረገመ ይሁን፤

4. ይህም ትእዛዝ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር፣ ከብረት ማቅለጫው ምድጃ ባወጣኋቸው ጊዜ ድምፄን ቢሰሙ፣ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቁ፣ እነርሱ ሕዝቤ፣ እኔም አምላካቸው እንድሆን የሰጠኋቸው ቃል ነው፤

5. ዛሬም እንደሆነው ሁሉ ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ለአባቶቻችሁ ለመስጠት የገባሁትን መሐላ እፈጽማለሁ።’ ”እኔም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሜን” ብዬ መለስሁ።

6. እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባዮች ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘የዚህን ኪዳን ቃል ስሙ፤ አድርጉትም፤

7. የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ “ታዘዙኝ” በማለት ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው።

8. እነርሱ ግን የክፉ ልባቸውን እልከኝነት ተከተሉ እንጂ አልታዘዙኝም፤ ጆሮአቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም፤ ስለዚህ እንዲከተሉት አዝዤአቸው ያላደረጉትን የዚህን ኪዳን ርግማን ሁሉ አመጣሁባቸው።’ ”

9. እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “በይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ዘንድ አድማ ተገኝቶአል።

10. ቃሌን መስማት ወዳ ልፈለጉት ወደ ቀድሞ አባቶቻቸው ኀጢአት ተመለሱ፤ ሊያገለግሏቸውም ሌሎችን አማልክት ተከተሉ። የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ኪዳን አፈረሱ።

11. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሊያመልጡት የማይችሉትን ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፤ ወደ እኔ ቢጮኹም አልሰማቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 11