ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 9:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ሰው ከእርሱ ጋር ለመከራከር ቢፈልግ፤ከሺህ ጥያቄ እንዱን እንኳ መመለስ አይችልም።

4. ጥበቡ ጥልቅ፣ ኀይሉም ታላቅ ነውና፤እርሱን ተቃውሞ ያለ አንዳች ጒዳት የሄደ ማን ነው?

5. ሳያውቁት፣ ተራሮችን ይነቅላቸዋል፤በቍጣውም ይገለብጣቸዋል።

6. ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፤ምሰሶዎቿንም ያንቀጠቅጣል።

7. ፀሓይን ያዛታል፤ አትወጣምም፤ከዋክብትንም በማኅተም ያሽጋል።

8. እርሱ ብቻውን ሰማያትን ዘርግቶአል፤በባሕርም ማዕበል ላይ ይራመዳል።

9. እርሱ የድብና የኦሪዮን፣የፕልያዲስና የደቡብ ከዋክብት ፈጣሪ ነው፤

10. የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮችን፣የማይቈጠሩ ታምራትንም ያደርጋል።

11. እነሆ! በአጠገቤ ሲያልፍ አላየውም፤በጐኔም ሲሄድ፣ ልገነዘበው አልችልም።

12. ቢነጥቅ፣ ማን ይከለክለዋል?‘ምን መሥራትህ ነው?’ የሚለውስ፣ ማን ነው?

13. እግዚአብሔር ቍጣውን አይመልስም፤ረዓብን የሚረዱ እንኳ ይሰግዱለታል።

14. “ታዲያ፣ ከእርሱ ጋር እሟገት ዘንድ፣ልከራከረውም ቃላት እመርጥ ዘንድ፣ እንዴት እችላለሁ?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 9