ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 9:13-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. እግዚአብሔር ቍጣውን አይመልስም፤ረዓብን የሚረዱ እንኳ ይሰግዱለታል።

14. “ታዲያ፣ ከእርሱ ጋር እሟገት ዘንድ፣ልከራከረውም ቃላት እመርጥ ዘንድ፣ እንዴት እችላለሁ?

15. ጻድቅ ብሆንም እንኳ፣ ልመልስለት አልችልም፤ዳኛዬን ምሕረት ከመለመን ሌላ ላደርግ የምችለው የለም።

16. ጠርቼው ‘አቤት!’ ቢለኝም፣ያዳምጠኛል ብዬ አላምንም።

17. በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፤ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል፤

18. ምሬትን አጠገበኝ እንጂ፣ለመተንፈስ እንኳ ፋታ አልሰጠኝም።

19. የኀይል ነገር ከተነሣ፣ እርሱ ኀያል ነው!የፍትሕም ነገር ከተነሣ፣ መጥሪያ ሊሰጠው የሚችል ማን ነው?

20. ንጹሕ ብሆን እንኳ፣ አንደበቴ ይፈርድብኛል፣እንከን የለሽ እንኳ ብሆን፣ በደለኛ ያደርገኛል።

21. “ያለ ነቀፋ ብሆንም እንኳ፣ስለ ራሴ ግድ የለኝም፤የገዛ ሕይወቴንም እንቃታለሁ።

22. ሁሉም አንድ ነው፤‘እርሱ ጻድቁንና ኀጥኡን ያጠፋል’ የምለውም ለዚህ ነው።

23. መዓት ወርዶ ድንገት ሰው ሲጨርስ፣በንጹሓን መከራ ይሣለቃል።

24. ምድር በክፉዎች እጅ ስትወድቅ፣እርሱ የፈራጆቿን ዐይን ይሸፍናል፤ታዲያ፣ ይህን ያደረገው እርሱ ካልሆነ ማን ሊሆን ይችላል?

25. “ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፣አንዳችም ደስታ ሳያይ ያልፋል።

26. ከደንገል እንደ ተሠራ ታንኳ፣ለመንጠቅ ቍልቍል እንደሚበር ንስር ይፈጥናል።

27. ‘ማጒረምረሜን እረሳለሁ፤ገጽታዬን ቀይሬ ፈገግ እላለሁ’ ብል፣

28. ንጹሕ አድርገህ እንደማትቈጥረኝ ስለማውቅ፣መከራዬን ሁሉ እፈራለሁ።

29. በደለኛ መሆኔ ካልቀረ፣ለምን በከንቱ እለፋለሁ?

30. ሰውነቴን በሳሙና ብታጠብ፣እጄንም በልዩ መታጠቢያ ባነጻ፣

31. ልብሴ እንኳ እስኪጸየፈኝ ድረስ፣በዐዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 9