ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 7:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “የሰው ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ተጋድሎ አይደለምን?ዘመኑስ እንደ ምንደኛ ዘመን አይደለምን?

2. የምሽትን ጥላ እንደሚመኝ አገልጋይ፣ደመወዙንም እንደሚናፍቅ ምንደኛ፣

3. እንዲሁ ከንቱ ወራት ታደሉኝ፣የጒስቍልና ሌሊቶችም ተወሰኑልኝ።

4. በተኛሁ ጊዜ ‘መቼ ነግቶ እነሣለሁ?’እላለሁ፤ ሌሊቱ ይረዝማል፤ እስኪነጋም እገላበጣለሁ።

5. አካሌ ቈስሎ ትልና ቅርፊት ለብሶአል፤ቈዳዬ አፈክፍኮአል፤ ቍስሌም አመርቅዞአል።

6. “ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይፈጥናል፤ያለ ተስፋም ያልቃል።

7. ሕይወቴ ትንፋሽ ያህል እንደሆነች አስብ፤ዐይኔም ከእንግዲህ ደስታን አያይም።

8. አሁን የሚያየኝ ሰው ዐይን ከእንግዲህ አያየኝም፤ትፈልገኛለህ፤ እኔ ግን የለሁም።

9. ደመና በኖ እንደሚጠፋ፣ወደ መቃብር የሚወርድም አይመለስም።

10. ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፤ስፍራውም ከእንግዲህ አያውቀውም።

11. “ስለዚህ ከቶ ዝም አልልም፤በመንፈሴ ጭንቀት እናገራለሁ፤በነፍሴም ምሬት አጒረመርማለሁ።

12. በላዬ ጠባቂ ታደርግ ዘንድ፣እኔ ባሕር ነኝን ወይስ የባሕር አውሬ?

13. አልጋዬ ያጽናናኛል፣መኝታዬም ማጒረምረሜን ይቀንስልኛል ባልሁ ጊዜ፣

14. አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፤በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤

15. ስለዚህ እንዲህ ሆኖ ከመኖር፣መታነቅና መሞትን እመርጣለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 7