ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 30:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. በዐለት መካከል በምድር ጒድጓድ፣በደረቅ ሸለቆ ዋሻ ውስጥ ለመኖር ተገደዱ።

7. በጫካ ውስጥ ያናፋሉ፤በእሾሃማ ቍጥቋጦ መካከልም ይታፈጋሉ።

8. ስማቸው የማይታወቅ አልባሌ ናቸው፤ከምድሪቱም ተባረዋል።

9. “አሁን ግን ልጆቻቸው በዘፈን ይሣለቁብኛል፤በእነርሱም ዘንድ መተረቻ ሆኛለሁ።

10. ይጸየፉኛል ወደ እኔም አይቀርቡም፤ያለ ምንም ይሉኝታ በፊቴ ይተፋሉ።

11. እግዚአብሔር የቀስቴን አውታር ስላላላውና በመከራም ስለ መታኝ፣በፊቴ መቈጠብን ትተዋል።

12. በቀኜ በኩል ባለጌዎች ሆ! ብለው ተነሡብኝ፤ለእግሬም ወጥመድ ዘረጉ፤የዐፈር ድልድልም አዘጋጁብኝ።

13. መንገድ ዘጉብኝ፤የሚገታቸው ሳይኖር፣ሊያጠፉኝ ተነሡ።

14. በሰፊ ንቃቃት ውስጥ እንደሚመጣ ሰው መጡብኝ፤በፍርስራሽም መካከል እየተንከባለሉ ደረሱብኝ።

15. በድንጋጤ ተውጫለሁ፤ክብሬ በነፋስ እንደሚወሰድ ተወስዶአል፤በሰላም መኖሬም እንደ ደመና እልም ብሎ ጠፍቶአል።

16. “አሁን ነፍሴ በውስጤ አለቀች፤የመከራ ዘመንም ይዞኛል።

17. ደዌ በሌሊት ዐጥንቴን ይበሳል፤የሚቈረጥመኝም ፋታ አይሰጠኝም።

18. እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ ልብሴን ጨምድዶአል፤በልብሴም ክሳድ አንቆ ይዞኛል።

19. እርሱ ጭቃ ውስጥ ጥሎኛል፤እኔም ከዐፈርና ከዐመድ አልተሻልሁም።

20. “እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ነገር ግን አልመለስህልኝም፤በፊትህም ቆምሁ፤ አንተ ግን ዝም አልኸኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 30