ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 22:10-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ድንገተኛ አደጋ ያናወጠህ፤ወጥመድም ዙሪያህን የከበበህ ለዚህ ነው።

11. እንዳታይ ጨለማ የሆነብህ፣ጐርፍም ያጥለቀለቀህ ለዚህ ነው።

12. “እግዚአብሔር ከፍ ባለው ሰማይ የሚኖር አይደለምን?በሩቅ ከፍታ ያሉትን ከዋክብት ያያል!

13. ይህም ሆኖ ሳለ እንዲህ አልህ፤ ‘እግዚአብሔር ምን ያውቃል?በእንዲህ ያለ ጨለማ ውስጥስ ይፈርዳልን?

14. በሰማይ ክበብ ላይ ሲራመድ፣እንዳያየን ጥቅጥቅ ያለ ደመና ይሸፍነዋል።’

15. ኀጢአተኞች በሄዱባት፣በጥንቷ መንገድ እንደ ተመላለስህ ትቀራለህን?

16. ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤መሠረታቸውም በጐርፍ ተወሰደ።

17. እግዚአብሔርንም ‘አትድረስብን!ሁሉን የሚችል አምላክም ምን ያደርግልናል?’ አሉ።

18. ቤታቸውን በመልካም ነገር የሞላው ግን እርሱ ነው፤ስለዚህ ከኀጢአተኞች ምድር እርቃለሁ።

19. “ጻድቃንም የእነዚያን ጥፋት አይተው ይደሰታሉ፤ንጹሓንም እንዲህ ብለው ያፌዙባቸዋል፤

20. በእርግጥ ጠላቶቻችን ጠፍተዋል፤ሀብታቸውም በእሳት ተበልቶአል።’

21. “ለእግዚአብሔር ተገዛ፤ ከእርሱም ጋር ሰላም ይኑርህ፤በረከትም ታገኛለህ።

22. ምክርን ከአፉ ተቀበል፤ቃሉንም በልብህ አኑር።

23. ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ ትጠገናለህ፤ክፋትን ከድንኳንህ ብታርቅ፣

24. የወርቅህን አንኳር ትቢያ ላይ፣የኦፊር ወርቅህንም ጥልቅ ሸለቆ ውስጥ ብትጥለው፣

25. ሁሉን ቻዩ አምላክ ወርቅ ይሆንልሃል፤ምርጥ ብር ይሆንልሃል።

26. በዚያ ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፤ፊትህንም ወደ እግዚአብርሔር ታቀናለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 22