ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኤልፋዝ

1. ቴማናዊው ኤልፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፤

2. “ጠቢብ ሰው በከንቱ ንግግር መልስ ይሰጣልን?ወይስ በምሥራቅ ነፋስ ሆዱን ይሞላል?

3. በማይረባ ቃል፣ፍሬ ቢስ በሆነም ንግግር ይከራከራልን?

4. አንተ ግን እግዚአብሔርን መፍራት ታጣጥላለህ፤አምልኮተ እግዚአብሔርን ትከለክላለህ።

5. ኀጢአትህ አፍህን ታስተምረዋለች፤የተንኰለኞችንም አነጋገር መርጠህ ትይዛለህ።

6. የሚፈርድብህ አንደበትህ እንጂ እኔ አይደለሁም፣የሚመሰክርብህም እኔ ሳልሆን የገዛ ከንፈርህ ነው።

7. “ለመሆኑ ከሰው ሁሉ ቀድመህ የተወለድህ አንተ ነህን?ወይስ ከኰረብቶች በፊት ተገኝተሃል?

8. በእግዚአብሔር የመማክርት ጉባኤ ላይ ነበርህን?ጥበብስ የተሰጠው ለአንተ ብቻ ነው?

9. እኛ የማናውቀው አንተ ግን የምታውቀው ምን ነገር አለ?እኛስ የሌለን አንተ ያለህ ማስተዋል የቱ ነው?

10. በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ፣የሸበቱ ሽማግሌዎች ከእኛ ጋር አሉ።

11. የእግዚአብሔር ማጽናናት፣በርጋታ የተነገረህ ቃል አነሰህን?

12. ልብህ ለምን ይሸፍታል?ዐይንህንስ ምን ያጒረጠርጠዋል?

13. በእግዚአብሔር ላይ እንድትቈጣ፣እንደዚህ ያለ ቃል ከአፍህ እንዲወጣ ያደረገህ ምንድን ነው?

14. “ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድን ነው?ጻድቅስ ይሆን ዘንድ፣ ከሴት የተወለደ ምንድን ነው?

15. እነሆ፤ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤ሰማያትም በእርሱ ፊት ንጹሓን አይደሉም።

16. ታዲያ፣ ክፋትን እንደ ውሃ የሚጠጣ!አስጸያፊና ርኩስ ሰውማ እንዴት ይታመን!

17. “አድምጠኝ፤ በግልጽ አስረዳሃለሁ፤ያየሁትንም እነግርሃለሁ፤

18. ጠቢባን ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን፤ሳይሸሽጉ የተናገሩትን አስረዳሃለሁ፤

19. ምድሪቱ ለአባቶቻቸው ተሰጠች፤በመካከላቸውም ባዕድ አልተቀመጠም፤

20. ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ፣ጨካኙም በተመደበለት ዘመን ሁሉ ይሠቃያል።

21. የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ላይ ይጮኻል፤በሰላም ጊዜ ቀማኞች አደጋ ያደርሱበታል።

22. ከጨለማ ወጥቶ ማምለጥ ይፈራል፤ለሰይፍም የተመደበ ነው።

23. የአሞራ እራት ለመሆን ይቅበዘበዛል፤የጨለማ ቀን መቅረቡን ያውቃል።

24. ጭንቀትና ሐዘን ያስፈራሩታል፤ለማጥቃት እንደ ተዘጋጀ ንጉሥም ያይሉበታል፤

25. እጁን በእግዚአብሔር ላይ አንሥቶአልና፤ሁሉን የሚችለውን አምላክም ደፍሮአል፤

26. ወፍራምና ጠንካራ ጋሻ አንግቦ፣ሊቋቋመው ወጥቶአል።

27. “ፊቱ በስብ ቢሸፈን፣ሽንጡ በሥጋ ቢደነድንም፣

28. መኖሪያው በፈራረሱ ከተሞች፣የፍርስራሽ ክምር ለመሆን በተቃረቡ፣ሰው በማይኖርባቸው ወና ቤቶች ውስጥ ይሆናል።

29. ከእንግዲህ ባለጠጋ አይሆንም፤ ሀብቱም አይቈይም፤ይዞታውም በምድር ላይ አይሰፋም።

30. ከጨለማ አያመልጥም፤ቅርንጫፎቹን ነበልባል ያደርቃቸዋል፤በእግዚአብሔርም እስትንፋስ ይወሰዳል።

31. በአጸፋው አንዳች አያገኝምና፤ከንቱን ነገር በመታመን ራሱን አያታልል።

32. ጊዜው ሳይደርስ ይጠወልጋል፤ቅርንጫፉም አይለመልምም።

33. ፍሬው በጮርቃነት እንደ ተለቀመበት የወይን ተክል፤አበባውም እንደ ረገፈበት የወይራ ዛፍ ይሆናል።

34. የዐመፀኞች ጉባኤ ትመክናለች፤የጉቦ ሱሰኞችም ድንኳን በእሳት ትበላለች።

35. መከራን ይፀንሳሉ፣ ክፋትንም ይወልዳሉ፤በሆዳቸውም ተንኰል ይጠነስሳሉ።”