ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 1:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እርሱም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት።

3. ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፣ ሦስት ሺህ ግመሎች፣ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎችና አምስት መቶ እንስት አህዮች ነበረ፤ እጅግ ብዙ ባሮችም ነበሩት፤ በምሥራቅ አገር ከሚኖሩትም ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሰው ነበረ።

4. ወንዶች ልጆቹም ተራ በተራ በየቤታቸው ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር እንዲበሉና እንዲጠጡ ሦስቱን እኅቶቻቸውን ይጋብዙ ነበር።

5. የግብዣው ጊዜ ካለፈ በኋላ ኢዮብ ልኮ ያስመጣቸውና፣ “ምናልባት ልጆቼ ኀጢአት ሠርተው እግዚአብሔርንም በልባቸው ረግመው ይሆናል” በማለት ጠዋት በማለዳ ስለ እያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያነጻቸው ነበር፤ ኢዮብ ይህን ዘወትር ያደርግ ነበር።

6. አንድ ቀን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ሊቆሙ በመጡ ጊዜ፣ ሰይጣንም መጥቶ በመካከላቸው ቆመ።

7. እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “ከወዴት መጣህ?” አለው።ሰይጣንም፣ “በምድር ሁሉ ዞርሁ፤ ወዲያና ወዲህም ተመላለስሁባት” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።

8. እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም” አለው።

9. ሰይጣንም፣ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰለት፣ “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን?

10. በእርሱና በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን? የበጎቹና የላሞቹ መንጋ ምድርን ሁሉ እስኪሞሉ ድረስ የእጁን ሥራ ባርከህለታል።

11. እስቲ፣ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 1