ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 1:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “እነሆ፤ እርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፤ እርሱን ራሱን ግን እንዳትነካው” አለው።ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።

13. አንድ ቀን የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፤

14. መልእክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በሬዎች እያረሱ፣ አህዮችም በአጠገባቸው እየጋጡ ሳሉ፣

15. ሳባውያን ጥቃት አድርሰውባቸው ይዘዋቸው ሄዱ፤ አገልጋዮቹንም በሰይፍ ገደሉ። እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ።”

16. እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፣ “የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወረደች፤ በጎችንና አገልጋዮችንም በላች፤ እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ” አለው።

17. እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፣ “ከለዳውያን በሦስት ቡድን መጥተው ጥቃት አደረሱ፤ ግመሎችህንም ይዘው ሄዱ፤ አገልጋዮቹን በሰይፍ ገደሉ፤ እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ” አለው።

18. እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው እየበሉና እየጠጡ ሳሉ፣

19. እነሆ፤ ታላቅ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጣ፤ የቤቱንም አራት ማእዘናት መታ፤ እርሱም በልጆቹ ላይ ወድቆ ገደላቸው። እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ።”

20. ኢዮብም ተነሣ፤ ልብሱን ቀደደ፤ ራሱን ተላጨ፤ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤

21. እንዲህም አለ፤“ዕራቍቴን ከእናቴ ማሕፀን ወጣሁ፤ዕራቍቴንም እሄዳለሁ። እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን።”

22. በዚህ ሁሉ፣ ኢዮብ አልበደለም፤ በእግዚአብሔርም ላይ ክፉ አልተናገረም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 1