ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 8:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እናንተም ከተደበቃችሁበት ትወጡና ከተማዪቱን ትይዛላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከተማዪቱን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋልና።

8. ከተማዪቱን ስትይዙም በእሳት አቃጥሏት፤ እግዚአብሔር ያዘዘውንም አድርጉ፤ እነሆ አዝዣችኋለሁ።”

9. ከዚያም ኢያሱ ሰዎቹን ላካቸው፤ እነርሱም ሄደው ከጋይ በስተ ምዕራብ በቤቴልና በጋይ መካከል ባለው ቦታ አደፈጡ፤ ኢያሱ ግን እዚያው ከሕዝቡ ጋር ዐደረ።

10. በማግስቱ ጧት ኢያሱ ማልዶ በመነሣት ወንዶቹን ሰበሰበ፤ እርሱና የእስራኤል አለቆችም ከፊት ሆነው እየመሯቸው ወደ ጋይ ወጡ፤

11. ከእርሱ ጋር የነበሩትም ተዋጊዎች በሙሉ ወጥተው ወደ ከተማዪቱ በመጠጋት ከፊት ለፊቷ ደረሱ፤ ከዚያም ከጋይ በስተ ሰሜን መካከል ካለው ሸለቆ ማዶ ሰፈሩ።

12. ኢያሱ ቀደም ብሎ አምስት ሺህ ሰው ያህል በመውሰድ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ፣ በቤቴልና በጋይ መካከል እንዲያደፍጡ አድርጎ ነበር።

13. ከከተማዪቱ በስተ ሰሜን የነበሩትንም፣ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ የሸመቁትንም ወታደሮች ሁሉ ስፍራ ስፍራቸውን እንዲይዙ አደረጋቸው፤ በዚያችም ሌሊት ኢያሱ ወደ ሸለቆው ሄደ።

14. የጋይ ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እርሱና የከተማዪቱ ወንዶች ሁሉ ማልደው በመገሥገሥ፣ እስራኤልን ለመውጋት ከዓረባ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ስፍራ መጡ፤ ንጉሡ ግን ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ ያደፈጠ ኀይል የሚጠባበቀው መሆኑን አያውቅም ነበር።

15. ኢያሱና እስራኤል በሙሉ ድል የተመቱ መስለው በመታየት፣ ወደ ምድረ በዳው ሸሹ።

16. የጋይ ሰዎች በሙሉ እንዲያሳድዷቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም አሳደዱት፤ በዚህ ሁኔታም የጋይ ሰዎች ከከተማዪቱ እንዲርቁ ተደረገ።

17. እስራኤልን ለማሳደድ ከጋይና ከቤቴል ያልወጣ ወንድ አልነበረም፤ ከተማዪቱንም ከፍተው ትተው እስራኤልን ማሳደድ ያዙ።

18. እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “ከተማዪቱን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፣ የያዝኸውን ጦር ወደ ጋይ አነጣጥር” አለው፤ ኢያሱም ጦሩን ወደ ጋይ አነጣጠረ።

19. ይህን እንዳደረገም ያደፈጡት ሰዎች ከተደበቁበት ስፍራ በፍጥነት ወጥተው ወደ ፊት ሮጡ፤ ገብተው ከተማዪቱን ያዟት፤ ወዲያውኑም በእሳት አቃጠሏት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 8