ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 8:24-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. እስራኤላውያን የጋይን ወንዶች ሁሉ ባሳደዷቸው ሜዳና ምደረ በዳ ከጨረሷቸውና እያንዳንዳቸውንም በሰይፍ ከፈጁ በኋላ፣ ወደ ከተማዪቱ ተመልሰው በዚያ ያገኙትን ሁሉ ገደሉ።

25. በዚያች ዕለት የጋይ ሰዎች ሁሉ አለቁ፤ የወንዶቹና የሴቶቹም ብዛት ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበር።

26. ኢያሱ በጋይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋቸው ድረስ ጦር ያነጣጠረባትን እጁን አላጠፈም ነበር።

27. እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት፣ በከተማዪቱ ያገኙትን እንስሳትና ምርኮ ብቻ ለራሳቸው አደረጉ።

28. ስለዚህ ኢያሱ ጋይን አቃጠላት፣ እስከ ዛሬ እንደሚታየውም ለዘላለም የዐመድ ቊልልና ባድማ አደረጋት።

29. የጋይንም ንጉሥ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ሬሳውንም እስኪመሽ ድረስ እዚያው እንዳለ ተወው፤ ፀሓይ ስትጠልቅም፣ ኢያሱ ሬሳውን እንዲያወርዱትና በከተማው በር ላይ እንዲጥሉት አዘዘ፤ የትልልቅ ድንጋይ ቊልልም ከመሩበት፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛል።

30. ከዚያም ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ።

31. መሠዊያዉንም የሠራው የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ፣ እስራኤላውያንን ባዘዛቸው መሠረት ሲሆን፣ ይህንም የሠራው በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ባልተጠረበና የብረት መሣሪያ ባልነካው ድንጋይ ነው፤ በዚህም ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ የኅብረት መሥዋዕትም ሠው።

32. ኢያሱም ሙሴ የጻፈውን የሕግ መጽሐፍ እስራኤላውያን እያዩ በድንጋዮች ላይ ቀረጸው።

33. እስራኤል በሙሉ መጻተኛውም ሆነ ተወላጁ፣ ሽማግሌዎቻቸውም ሆኑ ሹማምታቸው እንዲሁም ዳኞቻቸው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ተሸከሙት ሌዋውያን ካህናት ፊታቸውን አዙረው፣ በታቦቱ ግራና ቀኝ ቆመው ነበር። የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲባርኩ መመሪያ በሰጠ ጊዜ፣ አስቀድሞ ባዘዘው መሠረት፣ ግማሹ ሕዝብ በገሪዛን ተራራ፣ ግማሹ ደግሞ በጌባል ተራራ ፊት ለፊት ቆመ።

34. ከዚህ በኋላ ኢያሱ፣ የሕጉን ቃላት በሙሉ ማለትም በረከቱንና መርገሙን ሁሉ፣ ልክ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው አነበበ።

35. ኢያሱ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ሴቶች፣ ሕፃናትና በመካከላቸው የኖሩ መጻተኞች ባሉበት ያነበበው፣ አንድም ሳይቀር ሙሴ ያዘዘውን ቃል ሙሉ በሙሉ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 8