ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 8:21-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ኢያሱና እስራኤል ሁሉ ያደፈጠው ጦር ከተማዪቱን መያዙንና ጢሱ ወደ ላይ መውጣቱን ሲያዩ፣ ወደ ኋላ ተመልሰው በጋይ ሰዎች ላይ አደጋ ጣሉባቸው፤

22. ያደፈጡትም ሰዎች እንደዚሁ ከከተማዪቱ ወጥተው መጡባቸው፤ ስለዚህ እስራኤላውያን በዚያም በዚህም ስለ ከበቧቸው የጋይን ሰዎች ከመካከል አደረጓቸው፤ እስራኤላውያንም ሰዎቹን ፈጇቸው፤ አንድ እንኳ የተረፈ ወይም ያመለጠ አልነበረም፤

23. ነገር ግን የጋይን ንጉሥ ከነሕይወቱ ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።

24. እስራኤላውያን የጋይን ወንዶች ሁሉ ባሳደዷቸው ሜዳና ምደረ በዳ ከጨረሷቸውና እያንዳንዳቸውንም በሰይፍ ከፈጁ በኋላ፣ ወደ ከተማዪቱ ተመልሰው በዚያ ያገኙትን ሁሉ ገደሉ።

25. በዚያች ዕለት የጋይ ሰዎች ሁሉ አለቁ፤ የወንዶቹና የሴቶቹም ብዛት ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበር።

26. ኢያሱ በጋይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋቸው ድረስ ጦር ያነጣጠረባትን እጁን አላጠፈም ነበር።

27. እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት፣ በከተማዪቱ ያገኙትን እንስሳትና ምርኮ ብቻ ለራሳቸው አደረጉ።

28. ስለዚህ ኢያሱ ጋይን አቃጠላት፣ እስከ ዛሬ እንደሚታየውም ለዘላለም የዐመድ ቊልልና ባድማ አደረጋት።

29. የጋይንም ንጉሥ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ሬሳውንም እስኪመሽ ድረስ እዚያው እንዳለ ተወው፤ ፀሓይ ስትጠልቅም፣ ኢያሱ ሬሳውን እንዲያወርዱትና በከተማው በር ላይ እንዲጥሉት አዘዘ፤ የትልልቅ ድንጋይ ቊልልም ከመሩበት፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 8