ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 8:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ ሰራዊቱን ሁሉ ይዘህ በመውጣት ጋይን ውጋ፤ የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼሃለሁና።

2. በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረግኸውንም ሁሉ፣ በጋይና በንጉሥዋ ላይ ትደግመዋለህ፤ በዚህ ጊዜ ግን ምርኮውንና ከብቱን ለራሳችሁ ታደርጉታላችሁ፤ ታዲያ ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ የደፈጣ ጦር አዘጋጅ።”

3. ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ በሙሉ ጋይን ለመውጋት ወጡ፤ ኢያሱም ምርጥ ከሆኑት ተዋጊዎቹ ሠላሳ ሺህ ጦር አዘጋጅቶ በሌሊት ላካቸው፤

4. እንዲህ የሚል ትእዛዝም ሰጣቸው፤ “እነሆ፤ ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ ታደፍጣላችሁ፤ ከከተማዪቱ አትራቁ፤ ሁላችሁም ነቅታችሁ ተጠባበቁ፤

5. እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንጠጋለን፤ ሰዎቹ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሊወጉን ወደኛ ሲመጡ፤ እኛ ደግሞ እንሸሻለን፤

6. እነርሱም፣ ‘ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት አሁንም ከእኛ በመሸሽ ላይ ናቸው’ በማለት ከከተማዪቱ እስክና ርቃቸው ድረስ ይከታተሉናል፤ በዚህ ሁኔታ እኛም እንሸሻለን፣

7. እናንተም ከተደበቃችሁበት ትወጡና ከተማዪቱን ትይዛላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከተማዪቱን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋልና።

8. ከተማዪቱን ስትይዙም በእሳት አቃጥሏት፤ እግዚአብሔር ያዘዘውንም አድርጉ፤ እነሆ አዝዣችኋለሁ።”

9. ከዚያም ኢያሱ ሰዎቹን ላካቸው፤ እነርሱም ሄደው ከጋይ በስተ ምዕራብ በቤቴልና በጋይ መካከል ባለው ቦታ አደፈጡ፤ ኢያሱ ግን እዚያው ከሕዝቡ ጋር ዐደረ።

10. በማግስቱ ጧት ኢያሱ ማልዶ በመነሣት ወንዶቹን ሰበሰበ፤ እርሱና የእስራኤል አለቆችም ከፊት ሆነው እየመሯቸው ወደ ጋይ ወጡ፤

11. ከእርሱ ጋር የነበሩትም ተዋጊዎች በሙሉ ወጥተው ወደ ከተማዪቱ በመጠጋት ከፊት ለፊቷ ደረሱ፤ ከዚያም ከጋይ በስተ ሰሜን መካከል ካለው ሸለቆ ማዶ ሰፈሩ።

12. ኢያሱ ቀደም ብሎ አምስት ሺህ ሰው ያህል በመውሰድ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ፣ በቤቴልና በጋይ መካከል እንዲያደፍጡ አድርጎ ነበር።

13. ከከተማዪቱ በስተ ሰሜን የነበሩትንም፣ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ የሸመቁትንም ወታደሮች ሁሉ ስፍራ ስፍራቸውን እንዲይዙ አደረጋቸው፤ በዚያችም ሌሊት ኢያሱ ወደ ሸለቆው ሄደ።

14. የጋይ ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እርሱና የከተማዪቱ ወንዶች ሁሉ ማልደው በመገሥገሥ፣ እስራኤልን ለመውጋት ከዓረባ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ስፍራ መጡ፤ ንጉሡ ግን ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ ያደፈጠ ኀይል የሚጠባበቀው መሆኑን አያውቅም ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 8