ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 6:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሰባት ካህናት፣ ሰባት ቀንደ መለከት ተሸክመው በታቦቱ ፊት ይውጡ፤ በሰባተኛውም ቀን ካህናቱ መለከት እየነፉ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ይዙሩ።

5. የማያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ከፍ ያለ ጩኸት ያሰማ፤ ከዚያም የከተማዪቱ ቅጥር ይፈርሳል፤ ሕዝቡም ወደ ላይ ይወጣል፤ እያንዳንዱም ሰው በቀጥታ ይገባል።”

6. ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባት ካህናትም ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው።

7. ሕዝቡንም፣ “ወደ ፊት ሂዱ፤ ከተማዋን ዙሩ፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድመው ይሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ” ሲል አዘዛቸው።

8. ኢያሱም ለሕዝቡ ከተናገረ በኋላ፣ ሰባቱ ካህናት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው መለከታቸውን እየነፉ ወደ ፊት ቀደሙ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተከተላቸው።

9. የታጠቁ ተዋጊዎችም መለከት ከሚነፉት ካህናት ፊት ቀድመው ሲሄዱ፣ ደጀን የሆኑት ጠባቂዎች ደግሞ ታቦቱን ተከተሉ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ መለከቶቹ ባለማቋረጥ ይነፉ ነበር።

10. ኢያሱ ሕዝቡን፣ “የማሸበሪያ ጩኸት አታሰሙ፤ ድምፃችሁ ከፍ ብሎ አይሰማ፤ ጩኹ እስከምላችሁም ቀን ድረስ ከአፋችሁ አንዲት ቃል አትውጣ፤ የምትጮኹት ከዚያ በኋላ ነው” ሲል አዘዛቸው።

11. ስለዚህ ኢያሱ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው፣ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ እንዲዞሩ አደረገ። ከዚያም ሕዝቡ ወደ ሰፈር ተመልሰው ዐደሩ።

12. ኢያሱ በማግሥቱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ።

13. ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እየሄዱ፣ መለከቱን ባለማቋረጥ ይነፉ ጀመር፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም እነዚህን በመቅደም ሲሄዱ፣ የደጀን ጠባቂዎቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ታቦት ይከተሉ ነበር፤ ካህናቱም ሳያቋርጡ መለከት ይነፉ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 6