ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 4:12-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ፣ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእስራኤላውያን ፊት ቀድመው ተሻገሩ።

13. አርባ ሺህ ያህሉ ጦርና ጋሻቸውን ይዘው፣ ለውጊያ ዝግጁ ሆነው፣ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ።

14. በዚያች ዕለት እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤ ሕዝቡ ሙሴን እንዳከበሩት ሁሉ፣ ኢያሱንም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አከበሩት።

15. ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤

16. “የምስክሩን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ እዘዛቸው።”

17. ኢያሱም ካህናቱን “ከዮርዳኖስ ውጡ” ብሎ አዘዛቸው።

18. ካህናቱ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ከውሃው በመውጣት እግራቸው ደረቁን መሬት ልክ ሲነካ የዮርዳኖስ ውሃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፤ እንደ ቀድሞው ሁሉ ሞልቶ በዳሩ ሁሉ ይፈስ ጀመር።

19. የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ሕዝቡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ በኢያሪኮ ምሥራቃዊ ዳርቻ በጌልገላ ሰፈረ።

20. ኢያሱም ከዮርዳኖስ ወንዝ ያወጧቸውን ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች በጌልገላ ተከላቸው፤

21. እስራኤላውያንንም እንዲህ አላቸው፤ “ልጆቻችሁ ወደ ፊት፣ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው አባቶቻቸውን ቢጠይቁ፣

22. ‘እስራኤል ይህን ዮርዳኖስ በደረቅ ምድር ተሻገረ’ ብላችሁ ንገሯቸው፤

23. አኛ እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን እንዳ ደረቀው ሁሉ እናንተም እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ በፊታችሁ አደረቀው።

24. ይህን ያደረገውም፣ የእግዚአብሔር ክንድ ብርቱ መሆኑን የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንዲያውቁና እናንተም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለዘላለም እንድ ትፈሩ ነው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 4