ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 2:18-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ወደ ምድሪቱ በገባን ጊዜ፣ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረ ድሽበት መስኮት ላይ አስረሽ ካንጠለጠልሽው፣ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፣ ወንድሞችሽንና የአባትሽን ቤተ ሰዎች ሁሉ ወደ ቤትሽ ካመጣሻቸው ብቻ ነው።

19. ማንም ከቤትሽ ወጥቶ መንገድ ላይ ቢገኝ፣ ደሙ በራሱ ላይ ነው፤ እኛ አንጠየቅበትም፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር እቤት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከተነካ የደሙ ባለ ዕዳ እኛ እንሆናለን።

20. እኛ የምናደርገውን ብትናገሪ ግን፣ ካስማልሽን መሐላ ነጻ እንሆናለን።”

21. እርሷም፣ “ይሁን፤ ባላችሁት ተስማምቻለሁ” ስትል መለሰች፤ ከዚያም ሰደደቻቸው፤ እነርሱም ሄዱ፤ ቀይ ፈትሉንም በመስኮቷ ላይ አንጠለጠለችው።

22. እነርሱም ወጥተው ወደ ኰረብቶቹ ሄዱ፤ የሚከታተሏቸውም ሰዎች በየመንገዱ ሁሉ ላይ ፈልገውና አጥተው እስኪመለሱ ድረስ፣ ሦስት ቀን በዚያው ተሸሸጉ።

23. ሁለቱም ሰላዮች ተመለሱ፤ ከኰረብቶቹም ወርደው ወንዙን በመሻገር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ መጥተው ያጋጠማቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት።

24. ለኢያሱም፣ “በእርግጥ እግዚአብሔር ምድሪቱን በሙሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል፤ በዚያ የሚኖረውም ሕዝብ ሁሉ እኛን ከመፍራቱ የተነሣ ልቡ መቅለጡን አይተናል” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 2