ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 17:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ከዚያም በመቀጠል ድንበሩ በደቡብ በኩል ወደ ቃና ወንዝ ይደርሳል። በምናሴ ከተሞችም መካከል የኤፍሬም ከተሞች ነበሩ፤ ያም ሆኖ የምናሴ ድንበር የወንዙ ሰሜናዊ ክፍል ሲሆን፣ እስከ ባሕሩ ይዘልቃል።

10. በደቡብ በኩል ያለው ምድር የኤፍሬም ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ያለው ደግሞ የምናሴ ነበር፤ የምናሴ ግዛት እስከ ባሕሩ የሚደርስ ሲሆን፣ ሰሜናዊ ድንበሩ አሴር፣ ምሥራቃዊ ድንበሩ ደግሞ ይሳኮር ነው።

11. እንዲሁም በይሳኮርና በአሴር ውስጥ፤ ቤትሳን፣ ይብልዓም፣ የዶር ሕዝብ፣ ዓይን ዶር፣ ታዕናክና መጊዶ በዙሪያቸው ካሉ ሰፈሮቻቸው ጋር የምናሴ ነበሩ፤ ሦስተኛውም ናፎት ነው።

12. ይሁን እንጂ የምናሴ ዘሮች እነዚህን ከተሞች መያዝ አልቻሉም፤ ከነዓናውያን የያዙትን ላለመልቀቅ ቊርጥ ሐሳብ አድርገው ነበርና።

13. እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው፣ እንጂ ከዚያ ፈጽመው አላባረሯቸውም ነበር።

14. የዮሴፍ ዘሮች ኢያሱን፣ “ቊጥራችን ብዙ ነው፤ እግዚአብሔርም አብዝቶ ባርኮናል፤ ታዲያ እንዴት ርስታችን አንድ ዕጣና አንድ ድርሻ ብቻ ሆነ?” አሉት።

15. ኢያሱም መልሶ፣ “ቊጥራችሁ ይህን ያህል በዝቶ ኰረብታማው የኤፍሬም ምድር እስከዚህ የሚጠባችሁ ከሆነ፣ ወደ ፌሪዛውያንና ወደ ራፋይም ምድር ወጥታችሁ ደኑን ለራሳችሁ መንጥሩ” አላቸው።

16. የዮሴፍም ዘሮች፣ “ኰረብታማው አገር አይበቃንም፤ ደግሞም በሜዳው ላይ ያሉት በቤትሳንና በሰፈሮችዋ፣ እንዲሁም በኢይዝራኤል ሸለቆ የሚኖሩት ከነዓናውያን ሁሉ የብረት ሠረገሎች አሏቸው” አሉት።

17. ኢያሱ ግን ለዮሴፍ ዘሮች ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ቊጥራችሁ ብዙ፣ እጅግም ኀያል እንደመሆናችሁ ድርሻችሁ አንድ ብቻ አይሆንም፤

18. ነገር ግን ደን የለበሰው ኮረብታማው አገር የእናንተ ነው፤ ሄዳችሁ መንጥሩት፣ ዳር ድንበሩ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ከነዓናውያን የብረት ሠረገላ ቢኖራቸውና ብርቱዎች ቢሆኑም እንኳ ከዚያ ታስወጧቸዋላችሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 17