ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 15:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. በምሥራቅ በኩል ያለው ወሰናቸው ደግሞ የጨው ባሕር ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚሠርግበት ይደርሳል።በሰሜን በኩል ያለው ወሰንም የዮርዳኖስ ወንዝ ከሚሠርግበት የባሕር ወሽመጥ ይነሣና

6. ሽቅብ ወደ ቤትሖግላ ይወጣል፤ ከዚያም በሰሜናዊው ቤትዓረባ በኩል አድርጎ የሮቤል ልጅ የቦሀን ድንጋይ እስካለበት ይደርሳል።

7. ከዚያም ድንበሩ ከአኮር ሸለቆ ወደ ዳቤር ይወጣና ከወንዙ በስተ ደቡብ ባለው በአዱሚም መተላለፊያ ፊት ለፊት አድርጎ በስተ ሰሜን ወደ ጌልገላ ይታጠፋል፤ በዓይንሳሚስ ምንጭ በኩል አልፎም ወደ ዓይንሮጌል ይወጣል።

8. እንደዚሁም የሄኖምን ልጅ ሸለቆ አልፎ ይሄድና የኢያቡሳውያን ከተማ እስከ ሆነችው እስከ ኢየሩሳሌም ደቡባዊ ተረተር በመዝለቅ፣ በራፋይም ሸለቆ ሰሜን ጫፍ በኩል አድርጎ ከሄኖም ሸለቆ በስተ ምዕራብ ካለው ኰረብታ አናት ላይ ይደርሳል።

9. ከዚያም በመቀጠል ከተራራው አናት ተነሥቶ ወደ ኔፍቶ ምንጮች በማምራት፣ በዔፍሮን ተራራ ላይ ያሉትን ከተሞች አልፎ ይወጣና ቂርያትይዓሪም ተብሎ ወደሚጠራው ወደ በኣላ ቊልቊል ይወርዳል፤

10. ከዚያም ከበኣላ በምዕራብ በኩል አድርጎ ወደ ሴይር ይታጠፍና ክሳሎን ተብሎ በሚጠራው በይዓሪም ኰረብታ ሰሜናዊ ተረተር አልፎ ቊልቊል ወደ ቤትሳሚስ በመውረድ ወደ ተምና ይሻገራል።

11. ደግሞም በአቃሮን ሰሜናዊ ተረተር አድርጎ ወደ ሽክሮን ይታጠፍና በበኣላ ተራራ ላይ አልፎ እስከ የብኒኤል ይደርሳል፤ ከዚህ በኋላ ወሰኑ ባሕሩ ላይ ይቆማል።

12. የምድሪቱ ምዕራባዊ ወሰን የታላቁ ባሕር ጠረፍ ነው።እንግዲህ በየጐሣው የተደለደለውን የይሁዳን ሕዝብ በዙሪያው የከበቡት ወሰኖቹ እነዚሁ ናቸው።

13. ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከይሁዳ ድርሻ ላይ ከፍሎ ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ሰጠው፤ አርባቅም የዔናቅ አባት ነበረ።

14. ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ዘሮች ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ከኬብሮን አሳደዳቸው፤

15. ከዚያም በዳቤር ሕዝብ ላይ ዘመተ፤ ዳቤር ቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበር።

16. ካሌብ፣ “ቂርያትሤፍርን ወግቶ ለሚይዝ ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ።

17. ስለዚህ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዛት፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳን ዳረለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 15