ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 10:33-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

33. በዚህ ጊዜ የጌዝር ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት መጣ፤ ኢያሱ ግን አንድ እንኳ ሳያስተርፍ ንጉሡንና ሕዝቡን መታቸው።

34. ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከለኪሶ ወደ ዔግሎን አለፉ፤ ወጓትም።

35. በዚያኑ ዕለት ያዟት፤ በሰይፍም ስለት አጠፏት፤ በለኪሶ እንዳደረጉት ሁሉ እዚህም በውስጧ የሚገኙትን ፈጽመው ደመሰሷቸው።

36. ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከዔግሎን ወደ ኬብሮን ወጡ፤ ወጓትም።

37. ከተማዪቱንም ከንጉሥዋ፣ ከመንደሮቿና በውስጧ ካሉት ጋር ሁሉ አንድም ሰው ሳያስቀሩ በሰይፍ ስለት ፈጇቸው፤ በዔግሎን እንዳደረጉት ሁሉ እዚህም ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ ፈጽመው ደመሰሱ።

38. ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ኋላ ተመልሰው ዳቤርን ወጓት።

39. ከተማዪቱን፣ ንጉሥዋንና መንደሮቿን ይዘው በሰይፍ ስለት ፈጇቸው፤ በውስጧ ያለውንም ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ ደመሰሱ፤ በልብናና በንጉሥዋ እንዲሁም በኬብሮን ያደረጉትን ሁሉ እዚህም በዳቤርና በንጉሥዋ ላይ ደገሙት።

40. በዚህ ሁኔታም ኢያሱ ተራራማውን አገር ኔጌቭን፣ የምዕራቡን ቈላና የተራራውን ሸንተረሮች ጨምሮ ምድሪቱን በሙሉ ከነገሥታቷ ጋር ያዘ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት፣ እስትንፋስ ያላቸውን ሁሉ ፈጽሞ ደመሰሰ፤ ማንንም በሕይወት አላስቀረም፤

41. ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ እንዲሁም የጎሶምን ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ በሙሉ ያዘ።

42. ኢያሱ እነዚህን ሁሉ ነገሥታትና ምድራቸውን ያሸነፈው በአንድ ዘመቻ ብቻ ነበር፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ተዋግቶላቸዋልና።

43. ከዚህ በኋላ ኢያሱ ከመላው እስራኤላውያን ጋር ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 10