ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 1:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”

10. ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤

11. “ወደ ሰፈር ግቡ፤ ለሕዝቡም፣ ‘ስንቃችሁን አዘጋጁ፤ ከአሁን ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ትወርሳላችሁ’ በሏቸው።”

12. ኢያሱ የሮቤልን ነገድ፣ የጋድን ነገድና የምናሴን ነገድ እኩሌታ እንዲህ አላቸው፤

13. “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዲህ ሲል የሰጣችሁን ትእዛዝ አስቡ፤ ‘እግዚአብሔር አምላካችሁ ያሳርፋችኋል፤ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።”

14. ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ እንዲሁም ከብቶቻችሁ ሙሴ በሰጣችሁ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው ምድር ይቆዩ፤ ነገር ግን ተዋጊዎቻችሁ ሁሉ፣ ከነሙሉ ትጥቃቸው፣ ከወንድሞቻችሁ ቀድመው ይሻገሩ፤ እናንተም ከወንድሞቻችሁ ጐን ተሰለፉ።

15. ይህም፣ እግዚአብሔር እስኪያሳርፋቸውና ለእናንተም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነርሱም እግዚአብሔር አምላካችሁ የሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው። ከዚህ በኋላ እናንተም ተመልሳችሁ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የሰጣችሁን፣ በፀሓይ መውጫ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር ትወርሳላችሁ።”

16. እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ያዘዝኸንን ሁሉ እናደርጋለን፤ ወደምትልከንም ሁሉ እንሄዳለን።

17. ለሙሴ ሙሉ በሙሉ እንደታዘዝን ሁሉ፣ ለአንተም እንታዘዛለን፤ ብቻ እግዚአብሔር አምላክህ ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ፣ አሁንም ከአንተ ጋር ይሁን።

18. በትእዛዝህ ላይ የሚያምፅና ለቃልህ የማይታዘዝ ሁሉ ይገደል፤ ብቻ አንተ ጽና፤ አይዞህ፤ በርታ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 1