ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዩኤል 3:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “እነሆ፤ እነርሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች አነሣሣቸዋለሁ፤ እናንተም ያደረጋችሁትን በገዛ ራሳችሁ ላይ እመልስባችኋለሁ።

8. ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሰዎች ሸጣለሁ፤ እነርሱም መልሰው በሩቅ ላሉት ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።

9. በሕዝቦች መካከል ይህን ዐውጁ፤ለጦርነት ተዘጋጁ፤ተዋጊዎችን አነሣሡ፤ጦረኞችም ሁሉ ቀርበው ያጥቁ።

10. ማረሻችሁ ሰይፍ፣ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡት፤ደካማውም ሰው፣“እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል።

11. እናንት በዙሪያ ያላችሁ ሕዝቦች ሁላችሁ፤ፈጥናችሁ ኑ፤ በዚያም ተሰብሰቡ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ተዋጊዎችህን ወደዚያ አውርድ!

12. “ሕዝቦች ይነሡ፤ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ ፈጥነው ይውረዱ፤ዙሪያውን ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ላይ ልፈርድ፣በዚያ እቀመጣለሁና።

13. ማጭዱን ስደዱ፤መከሩ ደርሶአልና፤ኑ ወይኑን ርገጡ፤የወይን መጭመቂያው ሞልቶ፣ከጒድጓዶቹም ተርፎ ፈሶአልና፤ክፋታቸው እንደዚህ ታላቅ ነው።”

14. ብዙ ሕዝብ፣ በጣም ብዙ ሕዝብ፣ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ ተሰብስቦአል፤ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ፣ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና።

15. ፀሓይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ከዋክብትም ከእንግዲህ አያበሩም።

16. እግዚአብሔር ከጽዮን ጮኾ ይናገራል፤ከኢየሩሳሌም ያንጐደጒዳል፤ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል።

17. “ከዚያም እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር፣በቅዱሱ ተራራዬ በጽዮን እንደምኖር ታውቃላችሁ፤ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፤ከእንግዲህም ወዲያ ባዕዳን አይወሯትም።

18. “በዚያ ጊዜ ተራሮች፣ አዲስ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤ኰረብቶችም ወተት ያፈሳሉ፤በይሁዳ ያሉ ሸለቆዎች ሁሉ ውሃ ያጐርፋሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤት ምንጭ ይፈልቃል፤የሰጢምን ሸለቆ ያጠጣል።

19. ግብፅ ባድማ፣ኤዶምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤በምድራቸው ንጹሕ ደም በማፍሰስ፣በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ፈጽመዋልና።

20. ይሁዳ ለዘላለም፣ኢየሩሳሌምም ለትውልድ ሁሉ መኖሪያ ትሆናለች፤

21. ደማቸውን እበቀላለሁ፤በደለኛውንም ንጹሕ አላደርግም።” እግዚአብሔር በጽዮን ይኖራል!

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዩኤል 3