ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዩኤል 3:3-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. በሕዝቤ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ወንዶች ልጆችን በዝሙት አዳሪዎች ለወጡ፤ወይን ጠጅ ለመጠጣትም፣ሴቶች ልጆችን ሸጡ።

4. “ጢሮስና ሲዶና እንዲሁም እናንተ የፍልስጥኤም ግዛቶች ሁሉ ሆይ፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ምን አላችሁ? ስላደረግሁት ነገር ብድር ልትመልሱልኝ ነውን? የምትመልሱልኝ ከሆነ፣ በፍጥነትና በችኰላ እናንተ ያደረጋችሁትን በራሳችሁ ላይ መልሼ አደርግባችኋለሁ።

5. ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤ የተመረጠውንም ንብረቴን ተሸክማችሁ ወደ ቤተ መቅደሳችሁ አስገብታችኋልና።

6. ከገዛ ምድራቸው ልታርቋቸው፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሰዎች ለግሪኮች ሸጣችኋቸው።

7. “እነሆ፤ እነርሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች አነሣሣቸዋለሁ፤ እናንተም ያደረጋችሁትን በገዛ ራሳችሁ ላይ እመልስባችኋለሁ።

8. ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሰዎች ሸጣለሁ፤ እነርሱም መልሰው በሩቅ ላሉት ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።

9. በሕዝቦች መካከል ይህን ዐውጁ፤ለጦርነት ተዘጋጁ፤ተዋጊዎችን አነሣሡ፤ጦረኞችም ሁሉ ቀርበው ያጥቁ።

10. ማረሻችሁ ሰይፍ፣ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡት፤ደካማውም ሰው፣“እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል።

11. እናንት በዙሪያ ያላችሁ ሕዝቦች ሁላችሁ፤ፈጥናችሁ ኑ፤ በዚያም ተሰብሰቡ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ተዋጊዎችህን ወደዚያ አውርድ!

12. “ሕዝቦች ይነሡ፤ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ ፈጥነው ይውረዱ፤ዙሪያውን ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ላይ ልፈርድ፣በዚያ እቀመጣለሁና።

13. ማጭዱን ስደዱ፤መከሩ ደርሶአልና፤ኑ ወይኑን ርገጡ፤የወይን መጭመቂያው ሞልቶ፣ከጒድጓዶቹም ተርፎ ፈሶአልና፤ክፋታቸው እንደዚህ ታላቅ ነው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዩኤል 3