ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዩኤል 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የአንበጣ ሰራዊት

1. በጽዮን መለከትን ንፉ፤በቅዱሱ ተራራዬም የማስጠንቀቂያውን ድምፅ አሰሙ፤በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፤እርሱም በደጅ ነው።

2. ይህም የጨለማና የጭጋግ ቀን፣የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው።የንጋት ብርሃን በተራሮች ላይ እንደሚወጣ፣ኀያልና ብዙ ሰራዊት ይመጣል፤ከጥንት እንዲህ ዐይነት ከቶ አልነበረም፤በሚመጡትም ዘመናት እንዲህ ዐይነት ከቶ አይሆንም።

3. በፊታቸው፣ እሳት ይባላል፤በኋላቸውም ነበልባል ይለበልባል፤በፊታቸው ምድሪቱ እንደ ዔድን ገነት ናት፤በኋላቸውም የሚቀረው ባዶ ምድረ በዳ ነው፤ምንም አያመልጣቸውም።

4. መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፤እንደ ጦር ፈረስም ይጋልባሉ።

5. ገለባ እንደሚበላ እንደሚንጣጣ እሳት፣ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ኀያል ሰራዊት፣የሠረገሎችን ድምፅ የሚመስል ድምፅ እያሰሙ፣በተራሮች ጫፍ ላይ ይዘላሉ።

6. በእነርሱ ፊት ሕዝቦች ይርዳሉ፤የሁሉም ፊት ይገረጣል።

7. እንደ ተዋጊዎች ድንገት አደጋ ይጥላሉ፤እንደ ወታደሮችም ቅጥርን ይዘላሉ፤ከመንገዳቸውም ሳይወጡ፣አቅጣጫ ይዘው ይጓዛሉ።

8. እርስ በርሳቸው አይገፋፉም፤እያንዳንዱ መስመሩን ጠብቆ ይሄዳል፤መስመራቸውን ሳይለቁ፣መከላከያውን ሰብረው ያልፋሉ።

9. ከተማዪቱን ይወራሉ፤በቅጥሩም ላይ ይዘላሉ፤በቤቶች ላይ ዘለው ይወጣሉ፤እንደ ሌባም በመስኮት ይገባሉ።

10. ምድር በፊታቸው ትንቀጠቀጣለች፤ሰማይም ይናወጣል፤ፀሓይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ከዋክብትም ከእንግዲህ ወዲያ አያበሩም።

11. በሰራዊቱ ፊት፣ እግዚአብሔር ያንጐደጒዳል፤የሰራዊቱ ብዛት ስፍር ቊጥር የለውም፤ትእዛዙንም የሚያደርግ እርሱ ኀያል ነው፤ የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ፣እጅግም የሚያስፈራ ነው፤ማንስ ሊቋቋመው ይችላል?

ልባችሁን ቅደዱ

12. “አሁንም ቢሆን፣በጾም፣ በልቅሶና በሐዘን፣በፍጹም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር።

13. ልባችሁን እንጂ፣ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣ቊጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ፣ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገሥ ነውና።

14. በምሕረቱ ተመልሶ፣ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የሚሆነውን፣የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን እንዲተርፋችሁ፣በረከቱን ይሰጣችሁ እንደሆነ ማን ያውቃል?

15. በጽዮን መለከትን ንፉ፤ቅዱስ ጾምን ዐውጁ፤የተቀደሰን ጉባኤ ጥሩ።

16. ሕዝቡን ሰብስቡ፤ጉባኤውን ቀድሱ፤ሽማግሌዎችን በአንድነት አቅርቡ፤ሕፃናትን ሰብስቡ፤ጡት የሚጠቡትንም አታስቀሩ፤ሙሽራው እልፍኙን ይተው፣ሙሽሪትም የጫጒላ ቤቷን ትተው።

17. በእግዚአብሔር ፊት የሚያገለግሉ ካህናት፣በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አደባባይ መካከል ሆነው ያልቅሱ፤እንዲህም ይበሉ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አድን፤ርስትህን በአሕዛብ መካከል መተረቻ፣መሣቂያና መሣለቂያም አታድርግ፤ለምንስ በሕዝቦች መካከል፣‘አምላካቸው ወዴት ነው?’ ይበሉን።”

የእግዚአብሔር መልስ

18. እነሆ፤ እግዚአብሔር ስለ ምድሩ ይቀናል፤ስለ ሕዝቡም ይራራል።

19. እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል፤“እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅና ዘይት፣እስክትጠግቡ ድረስ እሰጣችኋለሁ፤የሕዝቦች መዘባበቻ አላደርጋችሁም።

20. “የሰሜንን ሰራዊት ከእናንተ አርቃለሁ፤ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር በማድረግ፣ወደ ደረቀውና ወደ ባድማው ምድር እገፋዋለሁ፤ግማቱ ይወጣል፤ክርፋቱም ይነሣል።”በእርግጥ እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎአል።

21. ምድር ሆይ፤ አትፍሪ፤ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤በእርግጥ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጎአል።

22. የዱር እንስሳት ሆይ፤ አትፍሩ፤መሰማሪያ መስኮቹ ለምልመዋልና፤ዛፎቹ ፍሬያቸውን አፍርተዋል፤የበለሱ ዛፍና የወይኑ ተክልም እጅግ አፍርተዋል።

23. የጽዮን ሰዎች ሆይ፤ ደስ ይበላችሁ፤በአምላካችሁ በእግዚአብሔር፣ ሐሤት አድርጉ፤የበልግን ዝናብ፣በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፤እንደ ቀድሞውም፣የበልግንና የጸደይን ዝናብ በብዛት ልኮላችኋል።

24. ዐውድማዎቹ በእህል ይሞላሉ፤መጥመቂያ ጒድጓዶችም፣ በአዲስ የወይን ጠጅና በዘይት ተሞልተው ያፈሳሉ።

25. “በመካከላችሁ የሰደድሁት ታላቁ ሰራዊት፣ትልልቁ አንበጣና ትንንሹ አንበጣ፣ሌሎች አንበጦችና የአንበጣው መንጋ የበላውን፣እነዚህ ሁሉ የበሏቸውን ዓመታት ዋጋ እመልስላችኋለሁ።

26. እስክትጠግቡ የምትበሉት ብዙ ምግብ ይኖራችኋል፤ድንቅ ነገሮችን ለእናንተ የሠራውን፣የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ታመሰግናላችሁ፤ሕዝቤም ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም።

27. ከዚያም እኔ በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፣እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደሆንሁ፣እንደ እኔም ያለ፣ ሌላ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ሕዝቤም ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም።

የእግዚአብሔር ቀን

28. “ከዚህም በኋላ፣መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፤ጒልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ።

29. በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ እንኳ፣መንፈሴን አፈሳለሁ።

30. ድንቆችን በሰማያት፣እንዲሁም በምድር፣ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ አሳያለሁ።

31. ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ፀሓይ ትጨልማለች፤ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች።

32. የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ፣እርሱ ይድናል፤ እግዚአብሔርም እንዳለው፣በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም፣መድኀኒት ይገኛል፤ከትሩፋኑም መካከል እግዚአብሔር የጠራቸው በዚያ ይገኛሉ።