ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዩኤል 1:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤

2. እናንት ሽማግሌዎች፣ ይህን ስሙ፤በምድሪቱም የምትኖሩ ሁላችሁ፣ አድምጡ፤በእናንተ ዘመን፣ ሆነ በአባቶቻችሁም ዘመን፣እንዲህ ዐይነት ነገር ሆኖ ያውቃልን?

3. ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤ልጆቻችሁ ለልጆቻቸው ይንገሩ፤ልጆቻቸውም ለሚቀጥለው ትውልድ ይንገሩ።

4. ከአንበጣ መንጋ የተረፈውን፣ትልልቁ አንበጣ በላው፤ከትልልቁ አንበጣ የተረፈውን፣ኵብኵባ በላው፤ከኵብኵባ የተረፈውን፣ሌሎች አንበጦች በሉት።

5. እናንት ሰካራሞች፤ ተነሡ፤ አልቅሱ፤እናንት የወይን ጠጅ ጠጪዎች ሁሉ፤ ዋይ በሉ፤ስለ አዲሱ የወይን ጠጅ ዋይ ብላችሁ አልቅሱ፤አፋችሁ ላይ እንዳለ ተነጥቃችኋልና።

6. ኀያልና ቊጥር ስፍር የሌለው ሕዝብ፣ምድሬን ወሮአታልና፤ጥርሱ እንደ አንበሳ ጥርስ፣መንጋጋውም እንደ እንስት አንበሳ መንጋጋ ነው።

7. የወይን ቦታዬን ባድማ አደረገው፤የበለስ ዛፎቼንም ቈራረጠ፤ቅርንጫፎቻቸው ነጭ ሆነው እስኪታዩ ድረስ፣ቅርፊታቸውን ልጦ፣ወዲያ ጣላቸው።

8. የልጅነት እጮኛዋን እንዳጣች ድንግል፣ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ።

9. የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቍርባን፣ ከእግዚአብሔር ቤት ተቋርጦአል፤ በእግዚአብሔርም ፊት የሚያገለግሉ፣ካህናት ያለቅሳሉ።

10. ዕርሻዎች ባዶአቸውን ቀርተዋል፤ምድሩም ደርቆአል፤እህሉ ጠፍቶአል፤አዲሱ የወይን ጠጅ አልቆአል፤ዘይቱም ተሟጦአል።

11. እናንት ገበሬዎች፣ ዕዘኑ፤እናንት የወይን ገበሬዎች፣ ዋይ በሉ፤ስለ ገብሱና ስለ ስንዴው አልቅሱ፤የዕርሻው መከር ጠፍቶአልና።

12. ወይኑ ደርቆአል፤የበለስ ዛፉም ጠውልጎአል፤ሮማኑ፣ ተምሩና እንኮዩ፣የዕርሻው ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ስለዚህ ደስታ፣ከሰው ልጆች ርቆአል።

13. ካህናት ሆይ፤ ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ፤እናንተ በመሠዊያው ፊት የምታገለግሉ፣ ዋይ በሉ፤እናንት በአምላኬ ፊት የምታገለግሉ፣ኑ፤ ማቅ ለብሳችሁ ዕደሩ፤የእህል ቊርባኑና የመጠጥ ቊርባኑ፣ከአምላካችሁ ቤት ተቋርጦአልና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዩኤል 1