ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 66:16-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. በእሳትና በሰይፍ፣ እግዚአብሔር ፍርዱን በሰው ሁሉ ላይ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር ሰይፍ የሚታረዱት ብዙ ይሆናሉ።

17. “ወደ አትክልት ቦታዎች ለመሄድና ከተክሎቹ አንዱን ለማምለክ ራሳቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፣ የዕሪያዎችንና የዐይጦችን ሥጋ፣ የረከሱ ነገሮችንም የሚበሉ ሁሉ የመጨረሻ ፍርዳቸውን በአንድነት ይቀበላሉ” ይላል እግዚአብሔር።

18. “እኔም ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ፣ መንግሥታትንና ልሳናትን ሁሉ ልሰበስብ እመጣለሁ፤ እነርሱም መጥተው ክብሬንም ያያሉ።

19. “በመካከላቸው ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም የተረፉትን አንዳንዶቹን ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፣ ወደ ፉጥ፣ ወደ ታወቁት ቀስተኞች ወደ ሉድ፣ ወደ ቶባልና ያዋን እንዲሁም ዝናዬን ወዳልሰሙትና ክብሬን ወዳላዩት ራቅ ወዳሉት ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በሕዝቦችም መካከል ክብሬን ይናገራሉ።

20. ለእግዚአብሔር ቍርባን እንዲሆኑ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ከየመንግሥታቱ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም በፈረስ፣ በሠረገላና በጋሪ፣ በበቅሎና በግመል ያመጧቸዋል” ይላል እግዚአብሔር። “እስራኤላውያን የእህል ቊርባናቸውን በሥርዐቱ መሠረት በነጹ ዕቃዎች ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ እነዚህንም ያቀርቧቸዋል።

21. እኔም ካህናትና ሌዋውያን ይሆኑ ዘንድ አንዳንዶቹን እመርጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

22. “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤

23. “ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤

24. “ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸው አይጠፋም፤ ለሰውም ዘር ሁሉ አስጸያፊ ይሆናሉ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 66