ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 66:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ከሚያጽናኑ ጡቶቿ፣ትጠባላችሁ፤ ትረካላችሁም፤እስክትረኩም ትጠጣላችሁ፤በተትረፈረፈ ሀብቷም ትደሰታላችሁ።”

12. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ ሰላምን እንደ ወንዝ ውሃ አፈስላታለሁ፤የመንግሥታትንም ብልጥግና እንደ ጅረት ውሃ አጐርፍላታለሁ፤ትጠባላችሁ፤ በዕቅፏም ትያዛላችሁ፤በጭኖቿም ላይ ትፈነድቃላችሁ።

13. እናት ልጇን እሹሩሩ እንደምትል፣እኔም እናንተን እሹሩሩ እላችኋለሁ፤በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ።

14. ይህን ስታዩ፣ ልባችሁ ሐሤት ያደርጋል፤ዐጥንቶቻችሁም እንደ ሣር ይለመልማሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ከባሮቹ ጋር መሆኑ ይታወቃል፤ቊጣው ግን በጠላቶቹ ላይ ይገለጣል።

15. እነሆ፤ እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል ይመጣል፤ሠረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤ንዴቱን በቍጣ፣ተግሣጹንም በእሳት ነበልባል ይገልጣል።

16. በእሳትና በሰይፍ፣ እግዚአብሔር ፍርዱን በሰው ሁሉ ላይ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር ሰይፍ የሚታረዱት ብዙ ይሆናሉ።

17. “ወደ አትክልት ቦታዎች ለመሄድና ከተክሎቹ አንዱን ለማምለክ ራሳቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፣ የዕሪያዎችንና የዐይጦችን ሥጋ፣ የረከሱ ነገሮችንም የሚበሉ ሁሉ የመጨረሻ ፍርዳቸውን በአንድነት ይቀበላሉ” ይላል እግዚአብሔር።

18. “እኔም ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ፣ መንግሥታትንና ልሳናትን ሁሉ ልሰበስብ እመጣለሁ፤ እነርሱም መጥተው ክብሬንም ያያሉ።

19. “በመካከላቸው ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም የተረፉትን አንዳንዶቹን ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፣ ወደ ፉጥ፣ ወደ ታወቁት ቀስተኞች ወደ ሉድ፣ ወደ ቶባልና ያዋን እንዲሁም ዝናዬን ወዳልሰሙትና ክብሬን ወዳላዩት ራቅ ወዳሉት ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በሕዝቦችም መካከል ክብሬን ይናገራሉ።

20. ለእግዚአብሔር ቍርባን እንዲሆኑ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ከየመንግሥታቱ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም በፈረስ፣ በሠረገላና በጋሪ፣ በበቅሎና በግመል ያመጧቸዋል” ይላል እግዚአብሔር። “እስራኤላውያን የእህል ቊርባናቸውን በሥርዐቱ መሠረት በነጹ ዕቃዎች ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ እነዚህንም ያቀርቧቸዋል።

21. እኔም ካህናትና ሌዋውያን ይሆኑ ዘንድ አንዳንዶቹን እመርጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

22. “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 66