ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 65:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “ነገር ግን እግዚአብሔርን ለተዋችሁት ለእናንተ፣የተቀደሰ ተራራዬን ለረሳችሁት፣‘ዕጣ ፈንታ’ ለተባለ ጣዖት ቦታ ላዘጋጃችሁት፣‘ዕድል’ ለተባለም ጣዖት ድብልቅ የወይን ጠጅ በዋንጫ ለሞላችሁት፣

12. ተጣርቼ ስላልመለሳችሁ፣ተናግሬ ስላልሰማችሁ፣በፊቴ ክፉ ነገር ስላደረጋችሁ፣የሚያስከፋኝን ነገር ስለ መረጣችሁ፣ለሰይፍ እዳርጋችኋለሁ፤ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ።”

13. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ባሮቼ ይበላሉ፤እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ባሮቼ ይጠጣሉ፤እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ባሮቼ ደስ ይላቸዋል፤እናንተ ግን ታፍራላችሁ።

14. ባሮቼ፣ከልብ በመነጨ ደስታ ይዘምራሉ፤እናንተ ግን፣ልባችሁ በማዘኑ ትጮኻላችሁ፤መንፈሳችሁ በመሰበሩም ወዮ ትላላችሁ።

15. ስማችሁንም፣የተመረጠው ሕዝቤ ርግማን እንዲያደርገው ትተዋላችሁ፤ጌታ እግዚአብሔር ይገድላችኋል፤ለአገልጋዮቹ ግን ሌላ ስም ይሰጣቸዋል።

16. ስለዚህ በምድሪቱ ላይ በረከትን የሚጠራ፣በእውነት አምላክ ስም ይባረካል፤በምድሪቱ መሐላን የሚምል፣በእውነት አምላክ ስም ይምላል፤ያለፉት ችግሮች ተረስተዋል፤ከዐይኖቼም ተሰውረዋል።

17. “እነሆ፤ እኔ፣አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤አይታወሱም።

18. ነገር ግን በምፈጥረው፣ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ።ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣ሕዝቧን ለሐሤት እፈጥራለሁና።

19. በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም።

20. “ከእንግዲህም በዚያ፣ለጥቂት ጊዜ ብቻ በሕይወት የሚኖር ሕፃን፣ወይም ዕድሜ ያልጠገበ አረጋዊ አይኖርም፤አንድ መቶ ዓመት የሞላው ሰው ቢሞት፣በአጭር እንደ ተቀጨ ይቈጠራል፤አንድ ሰው መቶ ዓመት ሳይሞላው ቢሞት፣እንደ ተቀሠፈ ይገመታል።

21. ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።

22. ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ወይም ሌላው እንዲ በላው አይተክሉም፤የሕዝቤ ዕድሜ፣እንደ ዛፍ ዕድሜ ይረዝማል፤እኔ የመረጥኋቸው፣በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።

23. ድካማቸው በከንቱ አይቀርም፤ዕድለ ቢስ ልጆችም አይወልዱም፤እነርሱና ዘራቸው፣ እግዚአብሔር የባረከው ሕዝብ ይሆናሉ።

24. ገና ሳይጣሩ እመልስላቸዋለሁ፤ተናግረው ሳይጨርሱ እሰማለሁ።

25. ተኵላና የበግ ጠቦት በአንድነት ይበላሉ፤አንበሳ እንደ በሬ ሣር ይበላል፤እባብ ትቢያ ይልሳል፤በተቀደሰው ተራራዬም፣ጒዳት አያደርሱም፤ ጥፋት አያመጡም፤”ይላል እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 65