ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 54:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እንደ ተናቀች የልጅነት ሚስት፣ከልብ እንዳዘነችና እንደ ተጠላች ሚስት፣ እግዚአብሔር እንደ ገና ይጠራሻል”ይላል አምላክሽ።

7. “ለጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፤ነገር ግን በታላቅ ርኅራኄ መልሼ እሰበስብሻለሁ።

8. ለጥቂት ጊዜ እጅግ ስለ ተቈጣሁ፣ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፤ነገር ግን በዘላለማዊ ቸርነቴ፣እራራልሻለሁ”ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር።

9. “ይህ ለእኔ የኖኅ ውሃ ምድርን ዳግመኛ እንዳያጥለቀልቃት እንደማልሁበት፣እንደ ኖኅ ዘመን ነው፤አሁንም አንቺን ዳግም እንዳልቈጣ፣እንዳልገሥጽሽም ምያለሁ።

10. ተራሮች ቢናወጡ፣ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም”ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።

11. “አንቺ የተጨነቅሽ ከተማ ሆይ፤ በዐውሎ ነፋስ የተናወጥሽ፣ ያልተጽናናሽም፤እነሆ፤ በከበሩ ድንጋዮች አስጊጬ እገነባሻለሁ፤በሰንፔር ድንጋይም እመሠርትሻለሁ።

12. ጒልላትሽን በቀይ ዕንቊ፣በሮችሽን በሚያብረቀርቁ ዕንቊዎች፣ቅጥሮችሽንም በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።

13. ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል።

14. በጽድቅ ትመሠረቻለሽ፤የግፍ አገዛዝ ከአንቺ ይርቃል፤የሚያስፈራሽ አይኖርም፤ሽብር ከአንቺ ይርቃል፤አጠገብሽም አይደርስም።

15. ማንም ጒዳት ቢያደርስብሽ፣ ከእኔ አይደለም፤ጒዳት ያደረሰብሽ ሁሉ ለአንቺ እጁን ይሰጣል።

16. “እነሆ የከሰሉ ፍም እንዲቀጣጠል የሚያራግበውን፣የጦር መሣሪያ የሚያበጀውን፣ አንጥረኛውን የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤ጥፋት እንዲያደርስም የፈጠርሁ እኔ ነኝአጥፊውንም የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤

17. በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው፤”ይላል እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 54