ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 54:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. “አይዞሽ አትፍሪ፤ ኀፍረት አይገጥምሽም፤ውርደት ስለማይደርስብሽ አትሸማቀቂ፤የወጣትነት ኀፍረትሽን ትረሺዋለሽ፤የመበለትነት ስድብሽንም ከእንግዲህ አታስታውሺውም።

5. ባልሽ ፈጣሪሽ ነውና፤ስሙም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ታዳጊሽ የእስራኤል ቅዱስ ነው፤እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል።

6. እንደ ተናቀች የልጅነት ሚስት፣ከልብ እንዳዘነችና እንደ ተጠላች ሚስት፣ እግዚአብሔር እንደ ገና ይጠራሻል”ይላል አምላክሽ።

7. “ለጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፤ነገር ግን በታላቅ ርኅራኄ መልሼ እሰበስብሻለሁ።

8. ለጥቂት ጊዜ እጅግ ስለ ተቈጣሁ፣ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፤ነገር ግን በዘላለማዊ ቸርነቴ፣እራራልሻለሁ”ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር።

9. “ይህ ለእኔ የኖኅ ውሃ ምድርን ዳግመኛ እንዳያጥለቀልቃት እንደማልሁበት፣እንደ ኖኅ ዘመን ነው፤አሁንም አንቺን ዳግም እንዳልቈጣ፣እንዳልገሥጽሽም ምያለሁ።

10. ተራሮች ቢናወጡ፣ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም”ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።

11. “አንቺ የተጨነቅሽ ከተማ ሆይ፤ በዐውሎ ነፋስ የተናወጥሽ፣ ያልተጽናናሽም፤እነሆ፤ በከበሩ ድንጋዮች አስጊጬ እገነባሻለሁ፤በሰንፔር ድንጋይም እመሠርትሻለሁ።

12. ጒልላትሽን በቀይ ዕንቊ፣በሮችሽን በሚያብረቀርቁ ዕንቊዎች፣ቅጥሮችሽንም በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።

13. ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 54