ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 49:5-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. በእግዚአብሔር ዐይን ፊት ከብሬአለሁ፤አምላኬ ጒልበት ሆኖልኛል፤ባሪያው እንድሆን ከማሕፀን የሠራኝ፣ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ፣እስራኤልን ወደ እርሱ እንድሰበስብ ያደረገኝ፣ እግዚአብሔር አሁንም እንዲህ ይላል፤

6. እርሱም፣“ባሪያዬ መሆንህ፣የያዕቆብን ነገዶች እንደ ገና መመለስህ፣የጠበቅኋቸውን እስራኤል መልሰህ ማምጣት ለአንተ ቀላል ነገር ነው፤ድነቴን እስከ ምድር ዳርቻ እንድታመጣ፣ለአሕዛብ ብርሃን አደርግሃለሁ” አለኝ።

7. እግዚአብሔር፣ታዳጊ የሆነው የእስራኤል ቅዱስ፣ለተናቀውና በሕዝብ ለተጠላው፣የገዦች አገልጋይ እንዲህ ይላል፤“ነገሥታት አይተውህ ይነሣሉ፤ልዑላንም አይተው፤ ይሰግዳሉ፤ምክንያቱም የመረጠህ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ታማኝ ነው።”

8. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በወደድሁ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤በድነትም ቀን እረዳሃለሁ።ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤

9. የተማረኩትን፣ ‘ኑ ውጡ’በጨለማ ያሉትን፣ ‘ነጻ ሁኑ’ እንድትል አድርጌሃለሁ።“በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤በተራቈተውም ኰረብታ ሁሉ ላይ መሰማሪያ ያገኛሉ።

10. አይራቡም፤ አይጠሙም፤የምድረ በዳ ትኵሳት ወይም የፀሓይ ቃጠሎ አይጐዳቸውም።የሚራራላቸው ይመራቸዋል፤በውሃ ምንጭ ዳርም ያሰማራቸዋል።

11. ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ።

12. እነሆ፤ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤አንዳንዶች ከሰሜን ሌሎች ከምዕራብ፣የቀሩት ደግሞ ከሲኒም ይመጣሉ።

13. ሰማያት ሆይ፤ እልል በሉ፤ምድር ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ተራሮች ሆይ፤ በደስታ ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያጽናናል፤ለተቸገሩትም ይራራልና።

14. ጽዮን ግን፣ “እግዚአብሔር ትቶኛል፤ጌታም ረስቶኛል” አለች።

15. “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን?ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን?ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣እኔ ግን እልረሳሽም።

16. እነሆ፤ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤ቅጥሮችሽ ምንጊዜም በፊቴ ናቸው።

17. ወንዶች ልጆችሽ ፈጥነው ይመለሳሉ፤ያፈራረሱሽም ከአንቺ ይሸሻሉ።

18. ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ።“በሕያውነቴ እምላለሁ፤እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር።

19. “ፈራርሰሽ ባድማ ብትሆኚ፣ምድርሽ ፈጽሞ ቢጠፋ፣ዛሬ ለሕዝብሽ ጠባብ ብትሆኚም እንኳ፣የዋጡሽ ከአንቺ ይርቃሉ።

20. በሐዘንሽ ዘመን የወለድሻቸው ልጆች፣ጆሮሽ እየሰማ፣‘ይህ ቦታ በጣም ጠቦናል፤የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይሉሻል።

21. በልብሽም እንዲህ ትያለሽ፣‘እነዚህን የወለደልኝ ማን ነው?እኔ ሐዘንተኛና መካን፣የተሰደድሁና የተጠላሁ ነበርሁ፤እነዚህን ማን አሳደጋቸው?ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ታዲያ፣ እነዚህ ከየት መጡ?’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 49