ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 49:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እናንት ደሴቶች ስሙኝ፤እናንት በሩቅ ያላችሁ ሕዝቦች ይህን አድምጡ፤በእናቴ ማሕፀን ሳለሁ እግዚአብሔር ጠራኝ፤ከመወለዴ በፊት በስም ጠራኝ።

2. አፌን እንደ ተሳለ ሰይፍ አደረገው፤በእጁ ጥላ ሰወረኝ፤የተወለወለ ፍላጻ አደረገኝ፤በሰገባውም ውስጥ ሸሸገኝ።

3. እርሱም፣ “እስራኤል፤ አንተ ባሪያዬ ነህ፤በአንተ ክብሬን እገልጣለሁ” አለኝ።

4. እኔ ግን፣ “ዐላማ ሳይኖረኝ እንዲሁ ደከምሁ፤ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ነገር ጒልበቴን ጨረስሁ፤ሆኖም ግን ብድራቴ በእግዚአብሔር እጅ፣ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው” አልሁ።

5. በእግዚአብሔር ዐይን ፊት ከብሬአለሁ፤አምላኬ ጒልበት ሆኖልኛል፤ባሪያው እንድሆን ከማሕፀን የሠራኝ፣ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ፣እስራኤልን ወደ እርሱ እንድሰበስብ ያደረገኝ፣ እግዚአብሔር አሁንም እንዲህ ይላል፤

6. እርሱም፣“ባሪያዬ መሆንህ፣የያዕቆብን ነገዶች እንደ ገና መመለስህ፣የጠበቅኋቸውን እስራኤል መልሰህ ማምጣት ለአንተ ቀላል ነገር ነው፤ድነቴን እስከ ምድር ዳርቻ እንድታመጣ፣ለአሕዛብ ብርሃን አደርግሃለሁ” አለኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 49