ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 49:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እናንት ደሴቶች ስሙኝ፤እናንት በሩቅ ያላችሁ ሕዝቦች ይህን አድምጡ፤በእናቴ ማሕፀን ሳለሁ እግዚአብሔር ጠራኝ፤ከመወለዴ በፊት በስም ጠራኝ።

2. አፌን እንደ ተሳለ ሰይፍ አደረገው፤በእጁ ጥላ ሰወረኝ፤የተወለወለ ፍላጻ አደረገኝ፤በሰገባውም ውስጥ ሸሸገኝ።

3. እርሱም፣ “እስራኤል፤ አንተ ባሪያዬ ነህ፤በአንተ ክብሬን እገልጣለሁ” አለኝ።

4. እኔ ግን፣ “ዐላማ ሳይኖረኝ እንዲሁ ደከምሁ፤ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ነገር ጒልበቴን ጨረስሁ፤ሆኖም ግን ብድራቴ በእግዚአብሔር እጅ፣ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው” አልሁ።

5. በእግዚአብሔር ዐይን ፊት ከብሬአለሁ፤አምላኬ ጒልበት ሆኖልኛል፤ባሪያው እንድሆን ከማሕፀን የሠራኝ፣ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ፣እስራኤልን ወደ እርሱ እንድሰበስብ ያደረገኝ፣ እግዚአብሔር አሁንም እንዲህ ይላል፤

6. እርሱም፣“ባሪያዬ መሆንህ፣የያዕቆብን ነገዶች እንደ ገና መመለስህ፣የጠበቅኋቸውን እስራኤል መልሰህ ማምጣት ለአንተ ቀላል ነገር ነው፤ድነቴን እስከ ምድር ዳርቻ እንድታመጣ፣ለአሕዛብ ብርሃን አደርግሃለሁ” አለኝ።

7. እግዚአብሔር፣ታዳጊ የሆነው የእስራኤል ቅዱስ፣ለተናቀውና በሕዝብ ለተጠላው፣የገዦች አገልጋይ እንዲህ ይላል፤“ነገሥታት አይተውህ ይነሣሉ፤ልዑላንም አይተው፤ ይሰግዳሉ፤ምክንያቱም የመረጠህ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ታማኝ ነው።”

8. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በወደድሁ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤በድነትም ቀን እረዳሃለሁ።ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤

9. የተማረኩትን፣ ‘ኑ ውጡ’በጨለማ ያሉትን፣ ‘ነጻ ሁኑ’ እንድትል አድርጌሃለሁ።“በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤በተራቈተውም ኰረብታ ሁሉ ላይ መሰማሪያ ያገኛሉ።

10. አይራቡም፤ አይጠሙም፤የምድረ በዳ ትኵሳት ወይም የፀሓይ ቃጠሎ አይጐዳቸውም።የሚራራላቸው ይመራቸዋል፤በውሃ ምንጭ ዳርም ያሰማራቸዋል።

11. ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 49