ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 45:5-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤ከእኔ በቀር አምላክ የለም።አንተ ባታውቀኝም እንኳ፣እኔ አበረታሃለሁ።

6. ይኸውም ሰዎች ከፀሓይ መውጫ፣እስከ መጥለቂያው፣ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ ነው፤እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም።

7. እኔ ብርሃንን ሠራሁ፤ ጨለማንም ፈጠርሁ፤አበለጽጋለሁ፤ አደኸያለሁ፤ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’

8. “እናንት ሰማያት፣ ጽድቅን ከላይ አዝንቡ፤ደመናትም ወደ ታች አንጠብጥቡ፤ምድር ትከፈት፤ድነት ይብቀል፤ጽድቅም አብሮት ይደግ፤እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።

9. “ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣ከሠሪው ጋር ክርክር ለሚገጥም ወዮለት፤ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን?የምትሠራውስ ሥራ፣‘እጅ የለህም’ ይልሃልን?

10. አባቱን፣‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣እናቱንም፣‘ምን ወለድሽ’? ለሚል ወዮለት።

11. “የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር፣ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን?ስለ እጆቼስ ሥራ ታዙኛላችሁን?

12. ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።

13. ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣ነጻ ያወጣል፤’ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”

14. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የግብፅ ሀብትና የኢትዮጵያ ንግድ፣ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች፣ወደ አንተ ይመጣሉ፤የአንተ ይሆናሉ፤ከኋላ ይከተሉሃል፤በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣በፊትህ እየሰገዱ፣‘በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 45