ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 45:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣ነጻ ያወጣል፤’ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”

14. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የግብፅ ሀብትና የኢትዮጵያ ንግድ፣ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች፣ወደ አንተ ይመጣሉ፤የአንተ ይሆናሉ፤ከኋላ ይከተሉሃል፤በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣በፊትህ እየሰገዱ፣‘በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።”

15. አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤አንተ በእውነት ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።

16. ጣዖት ሠሪዎች ሁሉ ያፍራሉ፤ ይቀላሉ፤በአንድነት ይዋረዳሉ።

17. እስራኤል ግን በእግዚአብሔር፣በዘላለም ድነት ይድናል፤እናንተም ለዘላለም፣አታፍሩም፤ አትዋረዱም።

18. ሰማያትን የፈጠረ፣እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣የመሠረታት፣የሰው መኖሪያ እንጂ፣ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ከእኔም በቀር ሌላ የለም።

19. በጨለማ ምድር፣በምስጢር አልተናገርሁም፤ለያዕቆብም ዘር፣“በከንቱ ፈልጉኝ” አላልሁም።እኔ እግዚአብሔር እውነትን እናገራለሁ፤ትክክለኛውንም ነገር ዐውጃለው።’

20. “በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤እናንት ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ።የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም።

21. ጒዳያችሁን ተናገሩ፤ አቅርቡ፤ተሰብስበውም ይማከሩ።ይህን አስቀድሞ ማን ዐወጀ?ከጥንትስ ማን ተናገረ?እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?ጻድቅና አዳኝ የሆነ አምላክ፣ከእኔ በቀር ማንም የለም፤ከእኔ ሌላ አምላክ የለም።

22. “እናንት የምድር ዳርቻ ሁሉ፣እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ።

23. ጒልበት ሁሉ በእኔ ፊት ይንበረከካል፤አንደበትም ሁሉ በእኔ ይምላል፤ብዬ በራሴ ምያለሁ፤የማይታጠፍ ቃል፣ከአፌ በጽድቅ ወጥቶአል።

24. ስለ እኔም ሲናገሩ፣ ‘ጽድቅና ኀይል፣ በእግዚአብሔር ብቻ ነው’ ይላሉ።”በእርሱ ላይ በቍጣ የተነሡ ሁሉ፣ወደ እርሱ መጥተው ያፍራሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 45