ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 42:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ።

13. እግዚአብሔር እንደ ኀያል ሰው ይዘምታል፤እንደ ተዋጊ በወኔ ይነሣል፤የቀረርቶ ጩኸት ያሰማል፤ጠላቶቹንም ድል ያደርጋል።

14. “ለረጅም ጊዜ ዝም አልሁ፤ጸጥ አልሁ፤ ራሴንም ገታሁ፤አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣እጮኻለሁ፤ ቁና ቁና እቃትታለሁ፤ እተነፍሳለሁ።

15. ተራራውንና ኰረብታውን አፈርሳለሁ፤ዕፀዋቱን ሁሉ አደርቃለሁ፤ወንዙንም ደሴት አደርጋለሁ፤ኵሬውን አደርቃለሁ።

16. ዕውሮችን በማያወቁት መንገድእመራቸዋለሁ፤ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ።ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ።ይህን አደርጋለሁ፤አልተዋቸውም።

17. በጣዖት የሚታመኑ ግን፣ምስሎችን፣ ‘አምላኮቻችን ናችሁ’ የሚሉ፣ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ ፈጽመው ይዋረዳሉም።

18. “እናንት ደንቈሮዎች ስሙ፤እናንት ዕውሮች እዩ፤ ተመልከቱም።

19. አገልጋዬ እንጂ፣ ሌላ ዕውር ማን አለ?ከምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ማን ደንቈሮ አለ?ለእኔ ታማኝ እንደሆነ ሰው የታወረ፣እንደ እግዚአብሔርስ አገልጋይ ዕውር ማነው?

20. ብዙ ነገርን አያችሁ፤ ነገር ግን አላስተዋላችሁም፤ጆሮአችሁ ክፍት ነው፤ ነገር ግን ምንም አትሰሙም።”

21. እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሲል፣ሕጉን ታላቅና የተከበረ በማድረግ ደስአለው።

22. ይህ ሕዝብ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ፣በጒድጓድ ውስጥ የተጠመደበት፣በወህኒ ቤት የተዘጋበት ነው፤ተበዝብዘዋል፣የሚያድናቸውም የለም፤ተማርከዋል፣“መልሷቸው” የሚልም የለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 42