ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 40:4-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፤ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ወጣ ገባው ምድር ይስተካከላል፤ሰርጓጒጡም ሜዳ ይሆናል።

5. የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፤ሰው ሁሉ በአንድነት ያየዋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።”

6. ድምፅም፣ “ጩኽ” አለኝ፤እኔም፣ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልሁ።“ሰው ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው።

7. ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነፍሶበታልና፤ሕዝቡ በርግጥ ሣር ነው።

8. ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

9. አንተ ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር፤ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤አንተ ለኢየሩሳሌም ብሥራት የምትነግር፣ድምፅህን ከፍ አድርገህ ጩኽ።ከፍ አድርገው፤ አትፍራ፤ለይሁዳም ከተሞች፣“እነሆ፤ አምላካችሁ!” በል።

10. እነሆ፤ ልዑል እግዚአብሔር በኀይልይመጣል፤ክንዱ ስለ እርሱ ይገዛል።እነሆ፤ ዋጋው ከእርሱ ጋር ነው፤የሚከፍለውም ብድራት አብሮት አለ።

11. መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል።

12. ውሆችን በዕፍኙ የሰፈረ፣ሰማያትን በስንዝሩ የለካ፣የምድርን ዐፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ተራሮችን በሚዛን፣ኰረብቶችንም በመድሎት የመዘነ ማነው?

13. የእግዚአብሔርን መንፈስ የተረዳ፣አማካሪውስ ሆኖ ያስተማረው ማነው?

14. ዕውቀት ለማግኘት እግዚአብሔር ማንን አማከረ?ትክክለኛውንስ መንገድ ማን አስተማረው?ዕውቀትን ያስተማረው፣የማስተዋልንም መንገድ ያሳየው ማን ነበር?

15. እነሆ፤ አሕዛብ በገንቦ ውስጥ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤በሚዛን ላይ እንዳለ ትቢያ ይቈጠራሉ፤ደሴቶችንም እንደ ደቃቅ ዐፈር ይመዝናቸዋል።

16. ሊባኖስ ለመሠዊያ እሳት አትበቃም፤የእንስሶቿም ቍጥር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያንሳል።

17. አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንደ ኢምንት ናቸው፤ከምንም የማይቈጠሩ መና ናቸው።

18. እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ?ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?

19. የተቀረጸውንማ ምስል ባለጅ ይቀርጸዋል፤ወርቅ አንጥረኛም በወርቅ ይለብጠዋል፤የብር ሰንሰለትም ያበጅለታል።

20. እንዲህ ያለውን መባ ማቅረብ የማይችል ምስኪን ድኻ፣የማይነቅዝ ዕንጨት ይመርጣል፤የማይወድቅ ምስልን ለማቆምም፣ታዋቂ ባለ ሙያ ይፈልጋል።

21. አላወቃችሁምን?አልሰማችሁምን?ከጥንት አልተነገራችሁምን?ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 40